አሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት ከፈፀመባቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች መካከል 40 የሚሆኑት ዳግም ስራ ጀመሩ

91

 ታህሳስ 12/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት ዘረፋና ውድመት ከፈፀመባቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች መካከል 40 የሚሆኑት ዳግም ስራ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ተናገሩ።

አሸባሪው ህወሃት ወረራ ፈፅሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሁሉ ባንኮችን፣ የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች የህዝብ መገልገያዎችን መዝረፉና ማውደሙ ይታወቃል።

የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂ ቡድን ወረራ አድርጎባቸው በነበሩ አካባቢዎች በ238 የባንኩ ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋና ውድመት መፈፀሙን የባንኩ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ቀደም ሲል መግለፃቸው ይታወሳል::

የሽብር ቡድኑ በርካታ የባንኩን ንብረቶች በመዝረፍና በማውደም፤ የኤቲ ኤም ማሽኖችን በየደረሰባቸው አካባቢዎች በመሰባበር ከፍተኛ ጉዳት ፈፅሟል።

አንድ የኤቲ ኤም ማሽን ለመትከል በግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ በመሆኑ በየአካባቢው የተፈፀመው ዘረፋና ውድመት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነው።

በሽብር ቡድኑ የተፈፀመው ዘረፋና ውድመት የከፋ ቢሆንም የባንኩን ቅርንጫፎች ዳግም ስራ ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።

በመሆኑም ዘረፋና ውድመት ከተፈፀመባቸው የባንኩ ቅርንጫፎች መካከል እስካሁን 40 የሚሆኑት ዳግም ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል ብለዋል።

በተያዘው ሳምንትም ሌሎች ተጨማሪ 20 ቅርንጫፎችን ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ በመቀሌ የሚገኙት 61 እና በሽሬ 59 የባንኩ ቅርንጫፎች ያሉበት ሁኔታ እስካሁን አይታወቅም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም