የፍቅር መገለጫ የሆነውን የገና በዓል የምናከብረው ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ካለን በማካፈል ሊሆን ይገባል

84

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 12/2014(ኢዜአ) የፍቅር መገለጫ የሆነውን የገና በዓል የምናከብረው ከቀያቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ካለን በማካፈል ሊሆን ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ።

የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ የሰሙና ከምስራቅ አገር በኮከብ ብርሃን ተመርተው ወደ ቤተልሔም የመጡ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ለተወለደው ህጻን ወርቅ ፣ እጣንና ከርቤን በስጦታ ማበርከታቸውን የክርስትና እምነት ድርሳናት ያስረዳሉ።

ይህን ተከትሎ በገና በዓል ስጦታ የመለዋወጥ ልምድ ከእንኳን አደረሳችሁና ከመልካም ምኞት መግለጫነት ባሻገር ወዳጅነትን፣ ቤተሰባዊነትንና ጓደኝነትን በማጠናከር በሰዎች ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ እንዲኖር አድርጓል ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ዜጎች በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እጅግ አስቸጋሪ ህይወት እንዲመሩ ተገደዋል።

በዚህም የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ስጦታ ማበርከትና ወገንተኝነትን በተግባር ማሳየት እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የክርስትና ሃይማኖት አባቶች መልዕከት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት የቅርስ ፣ላይብረሪና ሙዚየም ዋና ኃላፊ መላከ ሰላም አባ ቃለጽድቅ (ዶክተር) እንደገለጹት አሁን ያለንበት ወቅት ድግስ የምናበዛበት አይደለም ይላሉ።

ገናን ጨምሮ በተከታታይ የሚመጡ በዓላት ሲከበሩ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና ድጋፍ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ማገዝ የእምነቱ አስተምሮ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያን ህብረት ፕሬዝዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ድጋፍን የሚሹና ስጦታ ሊበረከትላቸው የሚገባ በርካታ ዜጎች ይገኛሉ ነው ያሉት።

የገና በዓል የስጦታ በዓል መሆኑን እንደ አጋጣሚ በመውሰድ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን መደገፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ይህ ተግባር የፈጣሪን መንገድ መከተልና የሱን ቃል መፈጸምም ጭምር ነው ሲሉ አክለዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ የላዛሪስት ገዳም አስተዳዳሪ አባ አብነት አበበ፤ ተረዳድቶና ተካፍሎ መብላት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ በገንዘብና በአይነት መገደብ እንደሌለበት ገልጸው፤ ምዕመኑ ተጎጂዎቹን በመጠየቅና በማጽናናት ወገን እንዳላቸው እንዲሰማቸው ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም