አምስት ተቋማት ለመከላከያ ሠራዊት ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

56

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 11/2014(ኢዜአ ) ለአገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት ለመግለፅ አምስት ተቋማት ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አበረከቱ።

ድጋፉን ካደረጉት መካከል የኦሮሚያ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ከሶስት ዞኖች ያሰባሰባቸውን ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሰንጋ በሬዎችና በጎችን አስረክቧል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እና የስራ አመራር ኢንስቲትዩት ደግሞ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና 400 ሺህ ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በስሩ ካሉ ማኅበራት ያሰባሰበውን 3 ሚሊዮን ብር፣ የጉራጌ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያም በስሩ ካሉ ኮሌጆች ጋር በመሆን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሴት አመራሮችና ሠራተኞች ለሠራዊቱ ያበረከቱት የአይነት ድጋፍ ነው።

የተቋማቱ ተወካዮች ድጋፋቸውን ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ አስረክበዋል።

የኦሮሚያ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ፈይሳ እንደገለጹት በክልሉ 373 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ሃብት ተሰብስቧል።

ከዚሁ ውስጥ ዛሬ ከሶስት ዞኖች የተሰባሰበው ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ መደረጉንና በቀጣይም ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሴት አመራሮችና ሠራተኞች ለሠራዊቱ ስንቅ አዘጋጅተው ማምጣታቸውን የገለፁት ደግሞ የባለስልጣኑ የስልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ወይዘሮ አበዜ ሱለይማን ናቸው።  

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌም እንዲሁ ኮሚሽኑ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን የአይነትና የገንዘብ ድጋፉን ማበርከቱን ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ400 ሺህ ብር በላይ የምግብ፣ የአልባሳትና የቁሳቁስ ድጋፍ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የተቋሙ ሠራተኞች ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሠራዊቱ 61 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በዛሬው ድጋፍም ከስራ ተቋራጮችና ማኅበራት 3 ሚሊዮን ብር አሰባስቦ ማስረከቡን ገልጸዋል።

አሸባሪ ቡድኑ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማድረሱን አንስተው አገልግሎቱ ነፃ በወጡ አካባቢዎች መሰረተ ልማት እየጠገነ ኅብረተሰቡን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊም መምሪያው በስሩ ካሉ ኮሌጆች ጋር በመሆን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የተለያዩ እህሎችና የንፅህና መጠበቂያዎች ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።

ድጋፉን የተረከቡት የአገር መከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ፤ ለሠራዊቱ እየተደረገ ያለው ድጋፍ እየተጠናከረ መምጣቱን፣ ይህም ለሠራዊቱ ተጨማሪ ብርታት በመሆን ድሎች እንዲበራከቱ ማድረጉን ተናግረዋል።

የተገኘውን ድል ለመጠበቅና በቀጣይም ድል ለማስመዝገብ የተደረገው ድጋፍ የሞራል ስንቅ እንደሆነም ገልጸዋል።

ሚኒስትር ደኤታዋ ድጋፍ ላደረጉት ተቋማት ምስጋና አቅርበው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም