ለዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ባለሃብቶች ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ባለሃብቶች ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረጉ ነው

ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ) ለዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ባለሀብቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ተናገሩ።
"በልስቲ ነጋሳና ልጆቹ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር" ለህልውና ዘመቻው የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ዛሬ ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አስረክቧል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ማህበሩ በከተማው በንግድና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተሰማርቶ ለከተማዋ እድገት ከማገዙ ባለፈ ለዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
በሀገር ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለመቀልበስ እየተካሄደ ባለው ዘመቻም የከተማው ባለሃብቶች ተሳትፎ ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
በህልውና ዘመቻው ማህበሩ ቀደም ሲል የ500 ሺህ ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የባለሃብቱ ተሳትፎ ያልተቆጠበና የሚያኮራ መሆኑን ጠቁመው፣ "በድጋፉ ባለሀብቶች በአስቸጋሪ ወቅት ለወገንና ለሀገር ያላቸውን ተቆርቋሪነትና አለኝታነት በተግባር አሳይተዋል" ብለዋል።
ባለሃብቶች ለህልውና ዘመቻው ያደረጉትን ርብርብ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሊደግሙት እንደሚገባ ዶክተር ድረስ ጥሪ አቅርበዋል።
ዛሬ ድጋፍ ያደረገው ድርጅት ባለቤት አቶ መላኩ በልስቲ በበኩላቸው፤ በህልውና ዘመቻው ክልሉ ባደረገው ጥሪ መሰረት የ15 ሚሊዮን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
"በአሁኑ ወቅት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባደረገው ለዘመቻ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጥሪ መሰረት የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገናል" ብለዋል።
ወደ ፊትም በወራሪው ህወሓት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ማህበሩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ባለሃብቶችና ዲያስፖራው ማህበረሰብ የህልውና አደጋውን ለመቀልበስ ካደረጉት ጥረት ባልተናነሰ በመልሶ ማቋቋም ተግባርም እንዲሳተፉም መልዕክት አስተላልፈዋል።