የኢትዮጵያዊያን አንድነት መጠናከር የጥቁር ህዝቦችን ነጻነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ነው

55

ሶዶ ታህሳስ 11/2014 (ኢዜአ ) የኢትዮጵያውያን አንድነት መጠናከር በአፍሪካ ሀገራት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስና የጥቁር ህዝቦችን ነጣነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ አስተዳደርና ልማት አመራር ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር አሜን ዲያቆን ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያውያን አንድነት መጠናከር ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት የጣለ ነው።

 ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዥዎችን በጠንካራ አንድነት ድል በማድረግ ለመላው የአፍሪካ ህዝብ የነፃነት ተምሳሌት መሆናቸውን አውስተዋል ።

አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ለማንበርከክ በርካታ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ጫናዎች እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህም በሀገሪቱ የተፈጠረውን ግጭት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀማቸውን ገልጸዋል።

ሀገራቱ ለአሸባሪው ህወሓት ግልፅ የሆነ ድጋፍ በማድረግ ጦርነቱ እንዲባባስ እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያውያን አንድነት መጠናከር  ከራስ አልፎ በአፍሪካ ሀገራት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀልበስና የጥቁር ህዝቦች ነፃነትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ጠንካራ አንድነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ አኳያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ማሞ ኢሳያስ ናቸው።

ኢትዮጵያ ላይ በአንዳንድ ምዕራባውያን መንግስታት እየተደረገ ያለ አድሎአዊ አሰራርና ጫና አሁንም መቀጠሉን አንስተው፤  ሂደቱ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን መላው የአፍሪካ ሀገራትን ማዳከምን ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የአንዳንድ ምዕራባውያን አጀንዳ ማስፈፀሚያ የሆኑ አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ የኢትዮጵያን አንድነት የማፍረስ ዓላማ አንግበው እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

"በመሆኑም የእጅ አዙር ዘመናዊ ቅኝ ግዛት እሳቤን ለማስቆም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የታየው ጠንካራ አንድነት ለሀገሪቱ ብሎም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተስፋ ሰጪ ነው" ሲሉ ምሁሩ አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም