የአሸንዳ በዓል ተሳታፊ ልጃገረዶች ከሚያሳዩት አንድነትና ፍቅር መማር ይቻላል---ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
የአሸንዳ በዓል ተሳታፊ ልጃገረዶች ከሚያሳዩት አንድነትና ፍቅር መማር ይቻላል---ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

መቀሌ ነሐሴ 19/2010 የአሸንዳ በዓል ተሳታፊ ልጃገረዶች ባህላቸውን ጠብቀው ከሚያሳዩት አንድነትና ፍቅር መማር እንደሚቻል የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተደዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡ በመቀሌ ከተማ ለሶስት ቀናት በድምቀት ሲከበር የቆየውን የአሸንዳ በዓል ትናንት ማምሻውን ሲጠናቀቅ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፣የአሸንዳ ልጆች ከባድ ዝናብና ብርድ ተቋቁመው ባህላቸውን ጠብቀው ለማቆየት ያላቸውን ፅናት ያሳያል። በክልሉ ባህላዊና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው በዓላት የህዝቡ አንድነትና ፍቅር መገለጫዎች በመሆናቸው ተጠብቀውና ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ መንግስት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የክልሉ ህዝብ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲሰፍንና ተጠቃሚነቱን ያረጋገጠ ዘላቂ ልማትን እንዲኖር በየጊዜው የሚያሳየው አንድነት ተጠናክሮ እንደሚቀጠል የአሸንዳ ልጆች አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ መንግስት የህዝቡን ደህንነትና ሰላም መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ኑሮውን ለመለወጥ ወደሚያስችለው ምዕራፍ መሸጋገሪያ ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ደብረፅዮን ተናግረዋል። በአዲሱ ዘመን ወንድም ከሆነው የኤርትራ ህዝብ ጋር የተጀመረውን ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር የክልሉ መንግስት ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የአሸንዳ በዓል በትግራይ ክልል ከተሞችና ገጠር አካባቢዎች ልጃገረዶች ተውበውና ደምቀው ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚያከብሩት የነጻነት መገለጫ በዓላቸው ነው። በዓሉ ከዓመት ወደ ዓመት እየደመቀ በመምጣቱ ለቱሪዝም ልማት ተጨማሪ ዘርፍ እየሆነ ከመምጣቱም ባለፈ የህዝቦችን ትስስር በማጠናከር የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል። በበዓሉ ማጠናቀቂያ ስነስርዓት ወቅት ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ጨምሮ የተለያዩ የፈደራልና የክልል የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ ጎብኚዎች ፣ የአሸንዳ በዓል ተሳታፊ ልጃገረዶች ፣ የመቀሌ ከተማና አካባቢ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡