ኢትዮጵያውያን የመደጋገፍ ባህላቸውን ተፈናቃዮችን በማቋቋም ሊያስቀጥሉት ይገባል

66

ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 10/2014---በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ዜጎች የመደጋገፍ ባህላቸውን አጠናክረው ሊያስቀጥሉ ይገባል ሲሉ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።

በባህር ዳር ከተማና አካባቢው የሚገኙ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አካሂደዋል።

በስነስርአቱ ላይ የተገኙት የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ዶክተር ድረስ ሳህሉ በወቅቱ እንዳሉት ሙስሊሙ ማህበረሰብ  ለህልውና ዘመቻው ወቅቱ የሚጠይቀውን እገዛ እያደረገ ነው።


የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በፈጸመው ወረራ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ከጎናቸው ሆኖ በማገዝ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ  አሁን ላይም  ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


"በአገራችን የተከሰተው ችግር በእኛው ይፈታል" በሚል መርህ የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊያን የመደጋጋፍ ባህላቸውን ማስቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

"እርስ በርስ በመደጋገፍና በመተጋገዝ ያጋጠመንን ልብ ሰባሪ ችግር በማለፍ ታሪክ መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉም ተናግረዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉም የአቅሙን አስተዋጾ እንዲያደርግም ዶክተር ድረስ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው፣ "አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች ዜጎችን ከቄያቸው ከማፈናቀል ባለፈ የህዝብና የግለሰብን ንብረት ዘርፏል፤ አውድሟል" ብለዋል።ቡድኑ የአርሶ አደሩን የደረሰ ሰብል አጭዶ ከመውሰድ ባለፈ ያልቻለውን የእህል ክምር በማቃጠል አሳፋሪ ድርጊት መፈጸሙን የገለጹት ሸህ ሰይድ፣ የተከበሩ የእምነት ተቋማትንም ማርከሱን ተናግረዋል።

"ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለሟቋቋም በሚደረገው ጥረት ያለው ለሌለው በማካፈል የመረዳዳት ባህላችንን በተግባር ማሳየት ይገባል" ሲሉም አክለዋል።

የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም ለሌላ የሚተው ተግባር ባለመሆኑ ማንኛውም ዜጋ አስተዋፅኦ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።

"ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም፤ የሙስሊሙ ማህበረሰብም የበኩሉን አስተዋፅኦ ያደርጋል'' ያሉት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር እስልምና ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሃሰን ሙሳ ናቸው።

"እኛ እያለን ወንድሞቻችን ሊራቡና ሊቸገሩ አይገባም" በሚል ሁሉም ሳይሰስት የበኩሉን መደገፍ እንዳለበት ጠቁመው፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተለመደውን ድጋፍ በማድረግ አገራዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የመርሀ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ይደግ ማሩ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች በሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ርካሽ ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።

በወራሪው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቄያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሲባል መርሃ ግብሩ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ለመጭዎቹ ሁለት ሳምንታት  በ20 መስጊዶች  በሚካሄደው መርሀ ግብር 25 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱ ታውቋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የሀይማኖቱ መሪዎችና የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የመንዙማና የዱአ ስርአትም  ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም