የአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 235 ተማሪዎችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 235 ተማሪዎችን አስመረቀ
አዲስ አበባ ነሐሴ 19/2010 የአፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 235 ተማሪዎች አስመረቀ። ኮሌጁ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ካምፓስ ያሰለጠናቸው 326 ተማሪዎች ምረቃ ስነ -ስርዓት በጊዮን ሆቴል አካሄዷል። ኮሌጁ በ2010ዓ.ም ያስመረቃቸው ተማሪዎች በማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ደረጃ አራት የሰለጠኑ ናቸው። የኮሌጁ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ እስራኤል ካሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ባለፉት 19 አመታት በአዲስ አበባ፣ በሀዋሳ፣ በሻሸመኔ፣ በነቀምቴና በዲላ ካምፓሶች ከ 40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል። እንደ አቶ እስራኤል ገለጻ ኮሌጁ ባለፉት ዓመታት ከማስተማር በሻገር በጥናትና ማህበረሰብ አገልግሎቶች በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ለአብነትም በአዲስ አበባ የሚገኙ እድሮች በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሰጥ ማድረጉን ገልጸው የመዲናዋ እድሮች ምክር ቤት እንዲቋቋምም ያራሱን አሻራ ማስቀመጡን ተናግረዋል። በተለይ በ2000ዓ.ም ተከስቶ የነበረው የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም በአዲስ አበባ የሸማቾች ኀብረት ሥራ ማህበራት እንዲቋቋም ኮሌጂ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል። “ኮሌጁ ላለፉት 13 ዓመታት በተመሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት ላይ ሲሳተፍም ቆይቷል'' ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ በቀጣዩ ዓመት ለ20 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌደሬሽን ማህበራት ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው ተመራቂዎች የመንግሥትን ቅጥር ከመጠበቅ ይልቅ በራሳቸው ስራ ፈጣሪ ሆነው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አመልክተዋል። በተለይም ሙስናን ጨምሮ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ገልጸው ተመራቂዎች መሰል ችግሮችን በመታገል አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል። “ወደ ሥራው ዓለም ስትገቡ ውጤታማ እንድትሆኑ በኛ በኩል የሚጠበቅብንን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን'' ሲሉም ቃል ገብተዋል። በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫና ሜዳሊያ ሽልማቶች ተበርክቷል።