የጂንካ ወጣቶች ለሀገራቸው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የጂንካ ወጣቶች ለሀገራቸው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ናቸው

ጂንካ (ኢዜአ) ታህሳስ 10 /2014 ---በደቡብ ኦሞ ዞን የጂንካ ከተማ ወጣቶች ለሀገራቸው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ።
ኢትዮጵያ አሁን ካጋጠማት ችግር መውጣት የምትችለው ሁሉም የድርሻውን ሲወጣ በመሆኑ ሀገራቸው የምትጠብቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ቀንና ለሊት በየደረጃው ካሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በከተማ የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ ካሉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች መካከል ወጣት ወንድማገኝ አለማየሁ አንዱ ነው።
አካባቢያቸውንና ከተማቸውን ከአሸባሪው የህወሓት ተላላኪዎች ለመጠበቅ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባባር እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል።
ወጣቱ አክሎም " የምናርፈው፣ ልጆቻችንን የምናስተምረውና ለወግ ማዕረግ የምናበቃው ሀገር ስትኖር ነው" ብሏል።
በመሆኑም ለሀገር ደህንነትና ሰላም ሲባል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ወጣት ወንድማገኝ ገልጿል።
"ቀን ስንባዝን ውለን ማታ ማረፍና ለቤተሰብ በቂ ጊዜ መስጠት ቢኖርበንም ሰላም ይበልጣል ብለን ምሽቱን አካባቢያችንን ከህወሓት ተላላኪዎች እየጠበቅን ነው" ሲልም አክሏል።
ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን አካባቢያቸውን በመጠበቅ በጦር ግንባር በጀግነነት እየተፋለመ ላለው ጥምር የወገን ጦር የኋላ ደጀን በመሆኑ ደስተኛ እንደሆነም ተናግሯል።
ወጣት ስጦታው አጥላባቸው በበኩሉ "እኛ ከዝናብ፣ ከብርድና ከድካም ጋር ሆነን የአካባቢያችንን ጸጥታ ብንጠብቅም መከላከያ ሠራዊቱ እየከፈለው ካለው የሕይወት መስዋዕትነት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ነው" ብሏል።
በአሁኑ ወቅት የውስጥ ጠላቶችና አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ግብ ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ጠቅሷል።
"ኢትዮጵያን ከተደቀኑባት አደጋዎች መታደግ የሚቻለው ደግሞ ሁላችንም በምንችለው አቅም ሁሉ የድርሻችንን መወጣት ስንችል ነው" ብሏል።
ለህዝብና ለሀገር ህልውና በአውደ ውጊያ እየተዋደቀ ያለውን መከላከያ ሠራዊት ለማገዝ ሁሉም አካባቢውን ከመጠበቅ ጀምሮ በተለያዩ የደጀንነት ግንባሮች አስተዋጾ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝቧል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ለሀገር ሉዓላዊነት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በጦር ግንባር መሰለፋቸው የሞራል ስንቅ እንደሆነውም ገልጿል።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደሞ በዛብህ እንዳሉት፣ በዞኑ 10ሺህ ያህል ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ሆነው የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ ነው።
የወጣቶቹ አስተዋጽኦ መንግሥት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ገልጸዋል።
አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ድንገተኛና የኬላ ፍተሻዎች ሀሰተኛ የብር ኖቶች፣ 18 ኩንታል አደንዛዥ ዕፅ፣ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና ጥይቶች መያዛቸውንም አስረድተዋል።
ከዚህም ባሻገር ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ጥቆማ በማስረጃ ጭምር በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።