ከሚሰራበት ተቋም ዝርፊያ የፈፀመው የጥበቃ ሰራተኛ በእስራት ተቀጣ

118

ጭሮ ታህሳስ 9/2014 (ኢዜአ) የተጣለበትን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከሚሰራበት ተቋም 102 ሺህ ብር የሰረቀው የጥበቃ ሰራተኛ በ6 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት ተቀጣ፡፡

አቶ ፋንታ አስፋው የተባለው ግለሰብ ይሰራበት ከነበረው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደር ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም 102 ሺህ ብር መስረቁን በአቃቤ ህግ ማስረጃና አሻራ ምርመራ መረጋገጡን የጭሮ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ዮብሰን በቀለ  ገልጸዋል።

ዳኛው እንዳሉት የሰው ምስክርና የፎረንሲክ ማዕከል የጽሁፍ ማስረጃ በአቃቤ ህግ በኩል የቀረበ ሲሆን፤ ተጠርጣሪው የመንግስትን ሀብት ከሌብነት እንዲጠብቅ የተጣለበትን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው   ከመስሪያ ቤቱ 102 ሺህ ብር በስርቆት በመውሰድና ለግል ጥቅሙ በማዋል  ጥፋተኛ ሆኖ በማግኘቱ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሰጥቷል፡፡

በዚህም የጭሮ ወረዳ ፍርድ ቤት በ6 አመት ከ6 ወር ፅኑ  እስራት በይኖበታል ነው ያሉት፡፡

ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ባዋለው ችሎት ተጠርጣሪው  ጥፋተኛ መሆኑ በመረጋገጡ ውሳኔ መስጠቱን  ዳኛው አቶ ዮብሰን በቀለ አስታውቀዋል።

የጭሮ  ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ሚካኤል ዳኜ በበኩላቸው ለምርመራ አስቸጋሪና ውስብስብ በሆነ መንገድ  ባለፈው አመት ታህሳስ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 እስከ 7፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ የተከናወነው ይኸ የስርቆት  ወንጀል በአሻራ ምርመራ ወንጀለኛው ተጣርቶ እንደተደረሰበት ገልጸዋል፡፡

የስርቆት ወንጀሉ የተፈፀመው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ፋይናንስ ገንዘብ ያዥ የሆኑት ግለሰብ  በእለቱ ከመንግስት የባንክ አካውንት 102 ሺህ ብር አውጥተው የያዙበትን ቦርሳ በቢሯቸው ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠው ለምሳ በሄዱበት ወቅት የበር ቁልፍ ሳይሰበር በተመሳሳይ ቁልፍ ተከፍቶ መሰረቁን  በማስረጃ መረጋገጡን ኢንስፔክተር ሚካኤል አመልክተዋል፡፡

"የተፈጸመውን የስርቆት ወንጀል በረቀቀ መንገድ የተከናወነና በማስረጃ ለማጠናከርም አስቸጋሪ ስለነበር ፖሊስና አቃቢ ህግ ቀን ከሌሊት ምርመራ በማድረግ የስምንት ሰው አሻራ ናሙና ወደ አዲስ አበባ ፎረንሲክ ምርመራ ማዕከል ተልኮ እንዲጣራ በመደረጉ ከቦርሳው ጋር ንክኪ ያለው ተጠርጣሪ የመስሪያ ቤቱ  ጥበቃ ሰራተኛ  አቶ ፋንታ አስፋው መሆኑንም ተረጋግጧል "ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም