ዩኒሴፍ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የትምህርት ግብአቶችን ለጋምቤላ ክልል ድጋፍ አደረገ

59

ጋምቤላ፣ ታህሳስ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በጋምቤላ ክልል የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የተለየዩ የትምህርት ግብአቶች ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ትናንት ለክልሉ ያስረከቡት በዩኒሴፍ  የጋምቤላ ተጠሪ ዶክተር አብዱልሃቅ ዋዊድ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የትምህርት ተቋማት ግንባታን ጨምሮ የተለያየ ድጋፍ እያደረገ ነው።

በተያዘው የትምህርት ዘመን በክልሉ የአምስት ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት ግብዓቶችን ድጋፍ ማድረጉን  ጠቅሰዋል።

ዩኒሴፍ አሁን ያደረገው ከ7ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የግብዓት ድጋፍ የትምህርት ተቋማት በሌሉባቸው አካባቢዎች የሚያገለግሉ ተንቀሳቃሽ የትምህርት መስጪያ ድንኳኖች፣ በርቀት ትምህርትን ለመከታተል የሚስያስችሉ ራዲዮኖች እና የተማሪ ቦርሳዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተማሪ ንፅህና መጠበቂያ፣ የቅድመ መደበኛ የትምህርት "ኪቶች" እና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶችም በድጋፉ እንደሚገኙበት ዶክተር አብዱልሃቅ አመልክተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሳ ጋጃት፤ በክልሉ ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ተደራሽትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት ስኬት ዩኒሴፍ እያደረገ ላለው ድጋፍ  አመስግነዋል።

የተለገሱት የትምህርት ቁሶች በተለይም ባለፈው ክረምት በአንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በጎርፍ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን ችግር በማቃለል በኩል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም