ሴት ጋዜጠኞች ማህበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም የስንቅ ድጋፍ አድርገዋል

73

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 10/2014(ኢዜአ) አምስት ሴት ጋዜጠኞች ማህበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም ሀገርን ለማዳን በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የጸጥታ ሃይል 700 ሺህ ብር የሚገመት የስንቅ ድጋፍ አድርገዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን  አማካሪ ጋዜጠኛ ስመኝ ግዛው በባህር ዳር ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጸችው፤ የፀጥታ ሀይሉን ለማገዝ ማህበራዊ የትስስር ገፆችን በመጠቀም ያደረጉት የሃብት አሰባሰብ ውጤታማ  ነው።

ማህበራዊ የትስስር ገፆችን ለበጎ ዓላማ በማዋል ሀገርን ለማዳን በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የወገን ሃይል  ድጋፍ ለማድረግ አምስት ሆነው በመደራጀት ሃብት ማሰባሰብ እንደቻሉ ነው ያስታወቀችው።

አንድ መቶ ኩንታል በሶ ለማሰባሰብ አቅደው ወደ ስራ በመግባት በሃገር ውስጥና ውጭ የሚኖሩ  ኢትዮጵያውያን ሃሳባቸውን በመደገፍ ባደረጉት አስተዋጽኦ 400 ኩንታል በሶ ማዘጋጀታቸውን ተናግራለች።

ከተሰበሰበው ውስጥም 700 ሺህ ብር ግምት ያለው በሶ በባህር ዳር ከተማ በመገኘት ለፀጥታ ሃይሉ ተደራሽ እንዲሆን ማስረከባቸውን ገልጻለች።

''አንድ መቶ ኩንታል በሶ ለዘማች'' በሚል የማህበራዊ ትስስር ገፅን በመጠቀም የተጀመረው ሃብት የማሰባሰብ ስራ ከሚጠበቀው በላይ ውጤታማ እንደሆነ የገለጸችው ደግሞ የስራና  ክህሎት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ጋዜጠኛ  አዜብ ታምሩ ናት።

ለሃገሩና ህዝቡ ሲል በግንባር እየተፋለመ የሚገኘውን የጸጥታ ሃይል  አቅም በፈቀደ ማገዝና መደገፍ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብላለች።

ለዚህም ጠንካራ ትብብርና እገዛ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሳ፤ ማህበራዊ የትስስር ገፅን ተጠቅመው  ባደረጉት እንቅስቀሴ ከሃገር ወዳድ ኢትዮጰያውያን የተሰጣቸው ምላሽ አበረታች መሆኑን ትናገራለች።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ እታገኘሁ አደመ በበኩላቸው፤ ሴት ጋዜጠኞች  ሀገሩን ለማስከበር እየተዋደቀ የሚገኘው የፀጥታ ሃይልን በመደገፍ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።

ሴት ጋዜጠኞቹ  ማህበራዊ የትስስር ገፆችን  በመጠቀም ለሰራዊቱ ድጋፍ የሚሆን በሶ ማዘጋጀት መቻላቸው አርያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ በቀጣይም መላው ኢትዮጵውያን የፀጥታ ሃይሉንም ሆነ ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም ድጋፉን አጠናከሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

ሀገር ለማዳን  እየተዋደቁ ለሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ በማድረግ የኋላ ደጀንነታቸውን  እያረጋገጡ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም