በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አብሮነትን በማሳየት ህመማቸውን መጋራት ያስፈልጋል

85

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አብሮነትን በማሳየት ህመማቸውን መጋራት እንደሚያስፈልግ የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ አስገነዘቡ።

አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ጭካኔ የተሞላበት ሰብዓዊ ጉዳት አድርሷል ያሉት ዶክተር ጌዲዮን፤ የፍትህ ተቋማት እና የሙያ ማህበራቱ አብሮነትን በማሳየት የደረሰውን የውድመት ቁስል የጋራ መሆኑን ለማሳየት ያለመ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የፍትህ ተቋማት እና የሙያ ማህበራቱ ያሰባሰቡትን የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጥሬ ገንዘብና ሌሎች የአይነት ድጋፎችን ለአፋር ክልል ተጎጂዎች እንዲውል ሚኒስትሩ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ አስረክበዋል።

በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይልን ለማጥፋት አኩሪ የጀግንነት ተጋድሎ ተካሂዷል።

"ፍትህ የሚረጋገጠው አገር ሲኖር ነው" ያሉት ሚኒስትሩ፤ በፈረሰ ሀገር ላይ ግን ምንም አይታሰብምና አገርን ለማዳን በርካታ ጀግኖች የክብር መስዋትነት መክፈላቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም በአሸባሪ ቡድኑ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል የፍትህ ተቋማቱና ማህበራቱ የአይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉ የደረሰው ውድመትና ቁስል የጋራ መሆኑን ለማሳየት ያለመ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የፍትህ ተቋማቱና ማህበራቱ ለተጎጂዎችና ክልሉን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም  አረጋግጠዋል።

በተያያዘ ዜናም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በክልሉ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አንድ ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ  አበርክቷል።

የተቋሙ ተወካይ አቶ  ጥበቡ ቦጋለ፤ ተቋሙ ከዚህ ቀደም በመጀመሪያ ዙር አማራና አፋር ክልሎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በአፋር ክልል በሽብር ቡድኑ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አንድ ሚሊየን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፍር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ፤ ተቋማቱ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ላሳዩት አለኝታነትና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም