ቀጥታ፡

የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በመጪው ጥቅምት ለጎብኝዎች ክፍት ይሆናል

አዲስ አበባ ነሐሴ 19/2010 የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ለጎብኝዎች ክፍት ሊደረግ ነው። ማዕከሉ አዲስ አበቤዎች ሰርጋቸውን ጫካ ውስጥ እንዲያካሂዱ፣ ከተፋፈገ ከተማ ወጥተው ንጹህ አየር እንዲምጉ፣ ለጤናቸው ስፖርት እንዲሰሩና ተማሪዎች የዕጽዋት ብዝኃ ሕይወት ተግባር ተኮር ትምህርት እንዲያካሂዱ ያስችላል ተብሏል። በ2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትብብር በሰሜን ምዕራብ አዲስ አበባ ጉለሌና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞችን በማካለል የተቋቋመው የጉለሌ ዕጽዋት ማዕከል 706 ሄክታር ይሸፍናል። በኢትዮጵያ ብቸኛ የሆነው የዕጽዋት ማዕከል ሲቋቋም የአካባቢ ሥነ ምህዳር ጥበቃ፣ የዕጽዋት ምርምር፣ ለአገር በቀል ዕፅዋት ጥበቃና ምርምር፣ ለተግባር ተኮር ትምህርትና ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ዓላማ በመያዝ ነው። ከባህር ወለል በላይ ከ2ሺህ 600 እስከ 3ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘው ማዕከሉ መተንፈሻ ላጡ አዲስ አበቤዎች የወደፊት መተንፈሻ እንደሚሆን የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ይናገራሉ። በእንጦጦ ተራራ ሰንሰለት ላይ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት የተተከሉ የባሕር ዛፎች የተሞላ እንደነበር የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ማዕከሉ ከተቋቋበት ጊዜ ጀምሮ በተሰራው ስራ የባህር ዛፉን ስርጭት በመቀነስ በአገር በቀል ዕጽዋት እየተተካ ነው። ደጋማና ወይና ደጋ አየር ንብረት ባለው ስፍራ በርካታ አገር በቀል ዕጽዋት መኖሩን ጠቅሰው፤ ለታሪክ የተወሰነ ቦታ ለባሕር ዛፍ በማስቀመጥ ሌላውን የማዕከሉ ክፍል በአገር በቀል ዕጽዋት እንደሚተካ ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ከ6ሺህ በላይ አገር በቀል የዕጽዋት ዝርያዎች እንዳሉ የሚናገሩት በማዕከሉ የምርምር ክፍል አስተባባሪ ዶክተር ብርሃኑ በላይ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ማዕከሉ የዕጽዋቱን ዝርያዎች በማሰባሰብ የማላመድ ስራ ይሰራል። ያም ሆኖ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሁሉንም ማምጣት እንደማይቻል ገልጸው፤ ቅድሚያ የሚሰጠው ለብርቅዬና በመጥፋት ላይ ለሚገኙ ዕጽዋቶች ነው። ወደፊትም ማዕከሉ አሰባስቦ በምርመር ያላመዳቸውን ዕጽዋቶች በዝርያና በባህሪ በማባዛት መልሶ ዕጽዋቶቹ ወደተሰበሰቡበት አካባቢ የማሰራጨት ስራ እንደሚኖር ገልጸዋል። በማዕከሉ የግንዛቤ ማስፋፊያና የኢኮ ቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፈቃዱ አሰፋ እንዳሉት፤ በአገሪቱ የሚገኙ አገር በቀልና በመጥፋት ላይ የሚገኙ ዕጽዋትን በማስቀደም የሚሰበሰቡበት፣ ለምርምር የሚውሉበትና እንክብካቤ የሚደረግበት መካነ ዕጽዋት ነው። በዚህም ከመዋለ ሕጻናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የዕጽዋት ባህርያት፣ አይነትና ምንነት ተግባር ተኮር ትምህርት የሚያገኙበት እንዲሁም ለመዝናኛ ኢኮ ቱሪዝም አገልግሎት ይሰጣል። ከዚህም በተጨማሪ ለጤና እግር ጉዞና ስፖርት፣ ለፊልም ቀረጻ፣ ለሰርግና ሌሎች የመዝናናኛ ኢኮ ቱሪዝም አገልግሎት ክፍት ለማድረግ ተወስኗል። ማዕከሉን ባለፉት አምስት ዓመታት ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ማዕከሉን መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ ከነዚህም መካከል ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ናቸው። በእስካሁኑ የማስጎብኘት ሂደት በሰው ኃይልና የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ችግር እንደነበር ያነሱት አቶ ፈቃዱ፤ በ2011 ዓ.ም 40 ሺህ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ ዕቀድ ተይዟል። ለዕቅዱ ስኬትም ማዕከሉ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከባሕልና ቱሪዝም፣ ከአስጎብኝ ድርጅትችና መሰል ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል። ማዕከሉ እስካሁን ጎብኝዎችን ያስተናግድ የነበረው በተበጣጠሰ አካሄድ እንደነበር ገልጸው፤ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ መሟላት ያለባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በማሟላት ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ገልጸዋል። ማዕከሉን ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ የጎብኝዎች ማቆያ አዳራሾች፣ የዕጽዋትና ስጦታ መሸጫ ሱቆች፣ የምግብ ካፍቴሪዎች፣ የሰርግ አዳራሽና ሌሎች መሰረተ ልማት ቢያስፈልግም አሁን ባሉ መሰረተ ልማቶች አገልግሎቱን ለመጀመር መወሰኑን ጠቁመዋል። እስካሁንም የጎብኝዎች መመላለሻ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፤ ጊዜያዊ ሽንት ቤቶች፣ አንድ ሎጅ፣ 150 መኪኖችን የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያዎች መገንባታቸውን፣ ፓርኪንግ ተሰርቷል። በአሰራር ግድፈትና በኮንስትራክሽን ውል ችግሮች ማዕከሉ ያልተረከባቸውና በህግ ጉዳይ የተያዙ የካፍቴሪያ፣ ሬስቶራንትና ዕቃ መሸጫ ግንባታዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤  ጉዳዩ ሲጠናቀቅ የመሰረተ ልማት ችግሩ እንደሚቃለልም ተናግረዋል። በ2011 በጀት ዓመትም የስብስባ አዳራሽ፣ የጎብኝዎች መመላለሻ የውስጥ ለውስጥ እግረኛ መንገዶች፣ ዘጠኝ ሽንት ቤቶች፣ የውሃ ግድብ፣ ተጨማሪ የውስጥ ጎብኝዎች ማዕከሉንና አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ የሚያዩባቸው ሁለት ማማዎች ለመገንባት በጀት ተይዟል። ለጎብኝዎች መግቢያ የህብረተሰቡ አቅም ባገናዘበ መልኩ ክፍያ እንደሚኖር የገለጹት አቶ ፈቃዱ፤ እንደመነሻ ለተማሪዎች 5 ብር፣ ለነዋሪዎች 10 ብር፣ እንዲሁም ለውጭ ዜጎች ደግሞ ከ25 እስከ 40 ብር በማዕከሉ ቦርድ መወሰኑን አንስተዋል። በተቋሙ ውስጥ የበጀት ችግር አለመኖሩን በመጥቀስ የባለሙያ አለመሟላትና የማዕከሉ አመራሮች የማስፈጽም አቅም ማነስ አሁን ድረስ ችግር ሆኖ መቆቱን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም