የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈጸመው ግፍ ልብ የሚሰብር ነው

64

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አሸባሪው ህወሓት ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች በሴቶች፣ ህፃናትና አቅመ ደካሞች ላይ የፈጸመው ግፍ ልብ የሚሰበር ነው" ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ነሲሴ ጫሊ ተናገሩ።

አሸባሪ ቡድን በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋና አስገድዶ መድፈር የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በአፋር ክልል ርዕሰ መዲና ሰመራ ተካሄዷል ።

ሰልፉን ያካሄዱት የሰመራ፣ ሎጊያ እና ዱብቲ ነዋሪዎች በጋራ በመሆን  ሲሆን፤ የሰልፉ ተሳታፊዎች ከአሸባሪ ቡድኑ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃገብነት አውግዘዋል፡፡

በሰልፉ "እኛ የአድዋ ጀግኖች ልጆች ነን አገራችን አናስደፍርም"፤ "ፆታ ተኮር ጥቃት አሁኑኑ ይቁም"፤ "በአፋርና አማራ ክልል የተፈጸመው ጥቃትና የጅምላ ጭፍጨፋ ፍትህ ያግኝ"፤ "ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ሰብዓዊ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የሚሰራጩት የተዛባ መረጃ ይቁም" የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡

የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ አሸባሪው ህወሃት ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሴቶች፣ ህፃናት እና አረጋዊያን  ላይ እየፈጸመው ጭፍጨፋ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ መሆኑ ተገልጿል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ነሲሳ ጫላ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት "እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው ሰልፍ አሸባሪ ቡድኑ በሴቶችና ህፃናት ላይ የፈጸመውን ግፍና መከራ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል በአፋርና በአማራ ክልሎች በእናቶች፣ በታዳጊ ህጻናት፣አካል ጉዳተኞችና አቅመ ደካሞች ላይ የፈጸመው ግፍ ልብ የሚሰብር መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ "ኢትዮጵያን እኔ ካልመራኋት አፈርሳታለሁ" በሚል ከንቱ ቅዠት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግፍ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያንም በተባበረ ክንድ የሽብር ቡድኑን ጥፋትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመመከት ረገድ እያሳዩት ያለውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል፡፡

በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተፈጠረው ትብብር በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም መደገም እንዳለበትም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ አኳያ ሴቶች ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ጥበብ ካላቸው ልምድ ጋር በማጣመር የበለጸገችና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመገንባት የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአፋር ክልል ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ኃላፊ አይሻ ያሲን፤ ኢትዮጵያዊያን የሽብር ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች የፈጸመውን ግፍ በአንድ ድምጽ እያወገዙት እንደሚገኙ አንስተዋል።

በአፋር ክልል ተገኝቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሴቶች በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሴቶችና ህጻናት ላይ የፈጸመው ግፍ የቡድኑን አረመኔነት በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

የአሻባሪ ቡድኑ ድርጊት የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይታሰብና እጅግ ልብ የሚሰብር መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም