ቀጥታ፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ሠራዊት የአከባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት ሥራ እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ ነሐሴ 19/2010 በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ሥር የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት የአከባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት ሥራ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ። የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ክልል መንግሥት በበኩሉ ሠራዊቱ በአከባቢው ከሚያደረገው የሠላም ማስከበር ተለዕኮ ጎን ለጎን የሚያካሄደው የልማት ሥራዎች አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን ገልጿል። የውኃ ቁፋሮ ዩኒት አዛዥ ሌተናል ኮለኔል ቴዎድሮስ ሃዱሽ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ የውኃ እጥረትን ለማቃለል አራት የመጠጥ ውኃ ጉድጓዶችን ቆፍረው ለአገልግሎት አብቅቷል። የውኃ ጉድጓዶቹ ለሠራዊቱ 30 ሺህ ሊትር በቀን ሲያቀርብ ለአከባቢው ማኅበረሰብ በተለይም ለባይደዋ ሆስፒታል በቀን አስር ሺህ ሊትር ውኃ እንደሚያቀርብ ነው ያስረዱት። የሠራዊቱ መቀመጫ ከሆነው ሥፍራ 60 ኪሎ ሜትር ላይም በሚትገኘው ቡራካባ ከተማ ላይ በቅርቡ አስር ሺ ሊትር የሚያቀርብ የውኃ ጉድጓድ መሰራቱንም ጠቅሰዋል።። የጉድጓድ ውኃን ለማጣራት በተተከለው መሣሪያ ላይ በባለሙያነት የሚያገለግሉት የሠራዊቱ አባላትም ሥራቸውን በተሳካ ሁኔታ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሻምበል ሰይፈዲን ሽኩር እንዳሉት የጉድጓዱን ዉሃ ቆፍረው እያጣሩ እየላኩ ነው፡፡ ሃምሳ አለቃ ስንታየሁ ይልማ ለሰራዊቱ ንጹኅ ዉሃ ለማቅረብ የማጣሪያ ማሽኖች መረከባቸውቸውን ገልጸው ሰራዊቱ ባሉበት ቦታ  ቦታ በቦቲ እንደሚያከፋፈሉ አስረድተዋል፡፡     ሠራዊቱ ከዚህ ጎን ለጎን የመንገድ ጥገናና የመንገድ ጥርጊያ ሥራ ላይም በርካታ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን መሥራቱን በሠራዊቱ የቀላል ኮንስትራክሽን ባለሙያ ሻምበል አስራት አሰፋ ይናገራሉ።   በተለይም ከዝናብ ጋር በተያያዘ ጎርፍና ከከባድ ጭቃ  ሠራዊቱ ለመንቀሰቀስ ችግር እንደሚገጥመው ገልጸው፤ በሠራዊቱ መኖሪያ ካምፕ ቅጥር ግቢ ውስጥ የውኃ ፍሳሽ መስመር ተሰርቷል ብለዋል።   ይህም ለሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን በተለይም ለደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ የሚያገለግለው ኤርፖርት መስመር የተሰራው መንገድ ለነዋሪውም ጭምር ያለው አዎንታዊ አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።   በቅርቡ የሚጠናቀቅም የሁለት ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ እድሳት ፕሮጀክት መጀመሩንም ባለሙያው ይናገራሉ።   የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ከልል የጤና ሚኒስትር ኢሳህ ማሃሙድ ሙርሳል በበኩላቸው በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሚካሄደው የልማት ሥራዎች የክልሉን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ያደርጋል።   ለሠራዊቱ መጠለያ የሆነው የባይደዋ ሆስፒታል በቀን አስር ሺህ ሊትር ውኃ ተጠቃሚ እንደሆነና ይህም ሆስፒታሉ የጤና አገልገሎት ሥራውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳው ገልጸዋል።   ጎን ለጎንም በተለይም ድንገተኛ የጤና አገልገሎት ሥራውን ለምሳሌ ያክልም ወረርሽኞች ሲከሰቱ በተደራጀ አኳኋን ለመሥራት  የሠራዊት እጀባ በማድረግም ሠራዊት ድጋፍ ማድረጉንም አንስተዋል።   በድምሩም የኢትዮጵያ ሠራዊት ለክልሉ ኅዝብ ቀላል የማይባል ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።   በአሚሶም ሥር የተሰማራው የኢትዮጵያ ሠራዊት በራሱ ወጪ ለአከባቢው ማኅበረሰብ የጤና አገልግሎትና ለሌሎች ተያያዥ የማኅበረሰብ ድጋፎች እንደሚያደርግም ለማወቅ ተችሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም