ህብረተሰቡ የስፔስ ሳይንስን እንዲገነዘብ ዘመናዊ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ ተግባራትን ማከናወን ያስፈልጋል

64
አዲስ አበባ ነሐሴ 19/2010 የስፔስ ሳይንስ የደረሰበትን እውቀት ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ በአገልግሎት ዘርፍ አስጠጥ ላይ ዘመናዊ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ተገለጸ። የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በየዓመቱ የሚሰጠውን የስፔስ ሳይንስ ግንዛቤ እየሰጠ ይገኛል። በግንዛቤ ማስጨበጫው ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ረመዳን ረሽድ እንደገለጹት፤ በአገሪቷ የስፔስ ሳይንስ የደረሰበትን እውቀት በማዳበር ውጤታማና ቀልጣፋ ተግባራትን ማከናወን ይገባል። የስፔስ ሳይንስን መረዳት የቴሌ ኮሙኒኬሽን፣የቴሌቪዥን፣ የራዲዮና የቦታ መጠቆሚያ (GPS) ሳተላይቶችን በመጠቀም የጤና፣ የትምህርት ስርዓትን፣ የከተሞችን አገልግሎት፣ የትራንፖርት ዘርፉን ለማዘመን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ስራ ለመስራት ያስችላል። ስለሆነም የዘንድሮው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ማንም ሰው በቤት ውስጥ በስፔስ ሳይንስ ላይ የሚያነሳቸውን ጥያቄ በመረጃ ላይ ተደግፎ መረጃ ለመስጠትና ተሰጥኦ ያላቸውን ህፃናት ደግሞ ስለ ስፔስ ሳይንስ ፍላጎቱ እንዲያድርባቸው ለማድረግ እንደሆነ ዶክተር ረመዳን ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛ ተስፋዬ ደግሞ ማህበሩ እስካሁን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በቀጣይ ከህብረተሰቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በተለይም መሬትን የሚመለከቱ፣ የመገናኛና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሳተላይቶች እንዲሁም የሳተላይት ሙዚየም ላይ ፕሮጀክቶች እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ህብረተሰቡ በስፔስ ሳይንስ ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማጎልበት ከሚሰሩ መደበኛ ስራዎች በተጨማሪ ኢ-መደበኛ የሆኑና ለሁሉም ሰው ዕድል የሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። የዘንድሮው መርሃ ግብር ሲዘጋጅ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን የአገር ቤትና ከውጭ የመጡ አቅራቢዎች ይሳተፉበታል ተብሏል። የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሩ ላይ 400 አዋቂዎችና ከ200 በላይ ህፃናት ልጆች እንደሚሳተፉ የተገለጸ ሲሆን የመሳተፍ ፍላጎት ያለው ሰው ሁሉ በመርሃ ግብሩ ላይ መሳትፍ ይችላል። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በ1996 ዓ.ም በ47 ግለሰቦች ተቋቁሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ የቆየ መሆኑንና በአሁኑ ሰአት በመላ አገሪቱ 20 ቅርጫፎችን ከፍቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም