ቀጥታ፡

የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያካሄደው ልዩ ስብሰባ ለኢትዮጵያ ፍጹም በጎ የማይመኙና ፖለቲካዊ አላማ ያላቸው አካላት አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዙሪያ ያካሄደው ልዩ ስብሰባ ለኢትዮጵያ ፍጹም በጎ የማይመኙና ፖለቲካዊ አላማ ያላቸው አካላት አጀንዳ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የኮሙኒኬሽኑ ሚኒሰትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች እና የተመድ የሰብአዊ መብቶች ም/ቤት በኢትዮጵያ ዙሪያ ያካሄደውን ልዩ ስብሰባ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው “የሽብር ቡድኑ በመሬት ላይ ሽንፈት ሲያጋጥመው በራሱና በላኩት በኩል ጩኸት ያሰማል ትላንት የሆነውም ይህ ነው” ብለዋል።

አሁንም ሰብአዊ መብት ጥሰት የሚል አጀንዳ ይዞ በመምጣት የራሱንና የላኩትን አካላት ፖለቲካዊ አጀንዳ በአለም አቀፍ ተቋማት ለማስፈጸም እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎችን የሰብአዊ ጉዳይ በተሟላ መልኩ ለማስፈጸም ጠንካራና ገለልተኛ የሆነ ተቋም የመመስረቱ ሂደት መከናወኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ባለፉት ሶስት አመታትም የዜጎች ሰብአዊ መብት እንዲጠበቅ ሰፊ ስራዎች መስራቱን ተናግረዋል።

ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመሆን ግልጽና ገለልተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ሪፖርት አድርገዋል ሲሉ አመልክተዋል።

ሆኖም “የፖለቲካ አጀንዳቸውን ማስፈጸም የሚፈልጉ አካላት ይህን አጀንዳ አድርገውታል፣ ፍጹም ለኢትዮጵያ በጎ የማይመኙና ፖለቲካዊ አጀንዳ ያላቻው አካላት ጉዳዩን አቀንቅነውታል” ሲሉ ገልጸዋል።

“ከአሸባሪው ህወሃት ወራራ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የጅምላ መቃብርና የሰብአዊ መብት ጥስት ሪፖርት ሲሰማ ጆሮ የሌላቸው እነዚህ አካላት አጀንዳውን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሲያደርጉት ነበር” ብለዋል።

የትላንቱ ጉዳይ ወስኖ ሸንጎ እንደ መግባት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ “ቀድሞውኑ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ወስነው የገቡ ናቸው” በማለትም አብራርተዋል።

“መንግስት ተመድን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ ስራዎችን ለመስራት ሰፊ ጥረትና የተግባር እንቅስቃሴ ቢያደርግም አሁን የተካሄደው ነገር ግን ቀደም ሲል ሲከናወኑ የነበሩ ነገሮችን ያበላሸ ነው” ብለዋል።

ይህ ሀሳብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ አካላት ሃሳብ ነው በዚህም መንግስት ውሳኔውን አይቀበለውም ነው ያሉት።

“የትላንቱ ሁኔታ ማን በፈተናዋ ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን አብሯት እንደሚቆምና ከጀርባ ሲያሴር እንደነበር የተመለከትንበት አጋጣሚ ነው፣ ታሪክ የሚዘክረው ወዳጆችን ያፈራንበት ነው ኢትዮጵያ ምስጋናዋን ታቀርባለች” ሲሉም አስታውቀዋል።

የአሸባሪውን ግፍና ወንጀል ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማድረስና መርጦ አልቃሾችን ለማጋለጥ መንግስት ይሰራልም ብለዋል።

“ኢትዮጵያ የጀመረችው ለውጥ ሰው ተኮር ነው የእያንዳንዱ ሰው መብት መከበርና መጠበቅን መንግስት ለማረጋገጥ ይሰራል” ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ።

-አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም