ተቋማቱ በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወጎኖች 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ አደረጉ

67

ታህሳስ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፍትህ ተቋማት እና ማህበራት አሸባሪው ህወሃት በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ እና የአይነት ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን ያደረጉት የፍትህ ሚኒስቴር፣ ዐቃቢያነ ህግና ሰራተኞች፣ የፌደራል ጠበቆች ማህበር እና የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር ናቸው።

ድጋፉንም የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ዛሬ በሰመራ ተገኝተው ለአፋር ክልል ፕሬዚደንት አወል አርባ አስረክበዋል።ክልሉን መልሶ በመገንባትና ወደ ልማት ለማስገባት በሚደረገው ርብርብ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በተያያዘ ዜናም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ በአፋር ክልል በሽብር ቡድኑ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል ሰብዓዊ ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉም የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ያካተተ ነው። የኮርፖሬሽኑ ተወካይ አቶ ጥበቡ ቦጋለ፤ ተቋሙ መረጃን ለማህበረሰቡ ከማድረስ በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሽብር ቡድኑ ተፈናቅለው ድጋፍ ለሚሹ የአማራ ወገኖች በደባርቅ፣ በደብረ ታቦር እና በሌሎች አካቢዎች ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አወል አርባ፤ “ሰይጣናዊ ባህሪ” በተላበሰው የህወሃት ወራሪ ኃይል ተፈናቅለው ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች አለኝታነታቸውን ለማሳየት ተቋማቱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም