የጥረት ኮርፖሬት ስምንት ፋብሪካዎች በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ውድመትና ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የጥረት ኮርፖሬት ስምንት ፋብሪካዎች በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ውድመትና ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል

ታህሳስ 8/2014/ኢዜአ/ ጥረት ኮርፖሬት በምስራቅ አማራ የሚገኙ ስምንት ፋብሪካዎቹ በአሸባሪው የሕወሃት ቡድን ውድመትና ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው አስታወቀ።
የአማራ ህዝብ የልማት ድርጅት በሆነው ጥረት ኮርፖሬት እህት ኩባንያዎች የአሸባሪው ህወሃት ቡድን የጥፋት እጆች ክፉኛ ካወደሟቸው ድርጅቶች መካከል ይገኝበታል።
የጥረት ኮርፖሬት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ መኮንን እንደተናገሩት፤ ጥረት ኮርፖሬት በምስራቅ አማራ በብረታ ብረት፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በውሃ፣ በማር ማቀነባበርና በሌሎች አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በግብርናና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እንዳሉት ገልጸዋል።
ከነዚህም መካከል በቀጣናው ከ3 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ ዕድል የፈጠሩ 8 አምራች ኢንዱስትሪዎች በአሸባሪው ቡድን ውድመትና ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው ነው የተናገሩት።
የአሸባሪ ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች ያደረሱት ጉዳት ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብን የመለወጥ ተስፋና ስነ ልቦና ላይ የተቃጣ ጥቃት ጭምር ነው ብለዋል።
በሁሉም ኢንዱስትሪዎች በተለይም ዋና ዋና ማሽነሪዎች፣ አሌክትሪካል ክፍሎች እና መለዋወጫዎች ጉዳት የተዳረጉ ሲሆን፤ አንዳንዶቹም ሙሉ በሙሉ አገልግሎት በማይሰጡበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አንዳንዶቹ ፋብሪካዎች የተወሰነ ጥገና ተደርጎላቸው መመለስ እንደሚችሉ ተስፋ የተጣለባቸው ቢሆንም ሌሎቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ በመውደማቸው በቀላሉ እንደማይመለሱ ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪዎችን ወደስራ ለማስገባትም የብድር፣ የውጭ ምንዛሬ እና ፈቃድ ነክ ልዩ መንግሰታዊ ድጋፎችን የሚሹ ናቸው ብለዋል።
በጥረት ኮርፖሬት እህት ኩባንያዎች መካከል በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኙት ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ፣ ዋልያ ቆርኬ ፋብሪካ እና ደሴ ስፕሪንግ ውሃ ይገኙበታል።
የድርጅቶቹ የስራ ኃላፊዎች እንዳረጋገጡት የህዝብ አንጡራ ሃብት የሆኑት ፋብሪካዎች በሽብር ቡድን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በደሴ ከተማ በስተሰሜን የሚገኘው የደሴ ሰፕሪንግ ውሃ ፋብሪካም ወደስራ መመለስ በማይችልበት ደረጃ ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን፤ በዚህም ከ150 እስከ 200 ሚሊየን ብር የሚገመት ሃብት ወድሞበታል።
የኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ጀማል 1 ሺህ 500 በላይ ሰራተኞች ያሉትና በዓመት ከ10 ሚሊየን ዶላር ገቢ የሚያስገኘው አንጋፋው ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ የጉዳት መጠኑ ለጊዜው ባይታወቅም ምርቶችና ንብረቶች ለዘረፋና ውድመት ተዳርገዋል ነው ያሉት።
የዋልያ ቆርኬ ፋብሪካ ስራ እስኪያጅ አቶ መላኩ ሰማኝ በበኩላቸው ፋብሪካው የራሱን ጥሬ ዕቃ በመጠቀም የሚያመርትና በኢትዮጵያ ብቸኛው የቆሮኬ ፋብሪካ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ከ80 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው ከ18 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ውድመት እንደደረሰበትም ነው የገለጹት፡፡