ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የሚተላለፉ ውሳኔዎች እንደማትቀበልና እንደማትተገብር አስታወቀች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የሚተላለፉ ውሳኔዎች እንደማትቀበልና እንደማትተገብር አስታወቀች
ታህሳስ 8 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የሚተላለፉ የትኛውም አይነት ውሳኔዎች እንደማትቀበልና እንደማትተገብር አስታወቀች።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ዙሪያ የጠራው ልዩ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።
በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ የናቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሁለቱ ተቋማት የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝና የሚኒስትሮች የጋራ ግብረ ሃይልም ተቋቁሞ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ ባለበት ሁኔታ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የጋራ ጥናቱን ወደ ጎን በመተው ይሄን ስብሰባ እንዲጠራ ማድረጉ የተወሰኑ ሃይሎች የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ልዩ ስብሰባው የጋራ ጥናቱን በመናቅ የጠራው ኢትዮጵያን የማተራመስ አጀንዳ ያለውና ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ የሚተላለፉ የትኛውም አይነት ውሳኔዎች እንደማትቀበል፣ እንደማትተገብርና ትብብር እንደማታደርግ ነው አምባሳደር ዘነበ ያስገነዘቡት።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት በስብሰባው ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ እንዲቃወሙና ውድቅ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ምክር ቤቱ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ሴቶች በመድፈር፣የጤናና የትምህርት ተቋማትንና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ዘረፋና ውድመት ሲፈጽም አለማውገዙና ዝምታን መምረጡ የምክር ቤቱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው ብለዋል።
ምክር ቤቱ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ ምርመራ ለማድረግ ፍላጎት አለማሳየቱና የፖለቲካ ጫና ለማሳደር እንደ መሳሪያነት መዋሉ የሚያሳዝን መሆኑን ነው አምባሳደር ዘነበ ያስረዱት።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን በመጀመሪያው የጋራ ሪፖርታቸው ያልዳሰሷቸውን የአማራና አፋር ክልሎች ላይ ምርምራ እንዲያደርግ ጥሪ ታቀርባለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና እንዲጠበቁ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ሊጭኑባት የፈለጉ ሃይሎችን ብቻዋን በዓለም መድረክ በመታገል አሸንፋለች አሁንም ከአጋሮቿ ጋር በመሆን ትግሏን ትቀጥላለች ብለዋል።