ቀጥታ፡

ወደ አገር ቤት ስንመጣ ''ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የለም'' የሚለውን የተሳሳተ መረጃ ከማጋለጥ ባሻገር ኢኮኖሚውን በተግባር እንደግፋለን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8/2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ሲመጣ ''ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የለም'' የሚለውን የተሳሳተ መረጃ ከማጋለጥ ባሻገር ኢኮኖሚውን በተግባር እንደሚደግፍ በአሜሪካ የዳላስና ቴክሳስ አካባቢ የጉዞ ወደ አገር ቤት አስተባባሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ለመምጣት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

በአሜሪካን አገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ በዳላስና ቴክሳስ አካባቢ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን የሚያስተባብረው ግብረ-ኃይል ተጠቃሽ ነው፡፡

የግብረ-ኃይሉ አስተባባሪ አቶ መላኩ ዳምጡ ከኢዜአ ጋር በበይነ-መረብ ባደረጉት ቆይታ፤ በዳላስና አካባቢዋ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት ለመምጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ወደ አገር ቤት ሲመጡም ከጉብኝት ባለፈ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያግዙ እቅዶችን ይዘው እንደሚመጡ አክለዋል፡፡

በተለይ ዳያስፖራው ይዞት የሚመጣውን የውጭ አገር ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲመነዝር እንደሚሰሩም ነው የገለጹት፡፡

በተጨማሪም በሽብር ቡድኑ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ በመገንባት ስራው ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ የፕሮጀክት ሃሳቦችን ይዘው እንዲመለሱ ከመንግስት አመራሮች ጋር የመወያየት እቅድ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ሌላኛው የግብረ-ኃይሉ አስተባባሪ አቶ ዘውገ ቃኘው በበኩላቸው፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች እያሳዩት ያለው አገር የመውደድና የአንድነት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

የተጀመረው ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ እንዲቀጥል ጠንክረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

"ወደ አገር ቤት ስንመጣ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም የለም የሚለውን የተሳሳተ ትርክት ከማጋለጥ ባለፈ በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እናበረክታለን" ብለዋል።

በአሜሪካ የተጀመሩ ሰልፎችን በተቀናጀ መልኩ ከመምራት አንስቶ አስከ ገንዘብ መዋጮ ያለው ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የግብረ ኃይሉ አስተባባሪ አቶ መላኩ ዳምጤ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን ንቅናቄ አፍሪካዊያን እንዲቀላቀሉት እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

በዳላስ የተጀመረው ወደ አገር ቤት የመምጣት እንቅስቃሴ በተመሳሳይ በዘጠኝ የአሜሪካን ከተሞች ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራበት መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም