ቀጥታ፡

ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በልዩ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል

ታህሳስ 8/2014/ኢዜአ/ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች በልዩ ሁኔታ ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታው ስለሺ ግርማ ለኢዜአ እንደተናገሩት በተለይም በቱሪስት መዳረሻዎችና የአገልግሎት ዘርፎች እንግዶቹን በልዩ ሁኔታ ተቀብለው እንዲያስተናግዱ የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

ይህንንም ተከትሎ የተዘጉ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች እንዲከፈቱና ጥገና የሚያስፈልጋቸውም ተገቢውን ጥገና እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ወደ ቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ሲያመሩ በትራንስፖርትና በሆቴል አገልግሎቶች ዘርፍ ከመደበኛው ዋጋ የ30 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ገልጸዋል።

የእነዚህ ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለአገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

በተለይም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በማሳየት ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል።

ይሀም ኢትዮጵያን በተመለከተ የተያዘውን የተዘባ ምልከታ እንዲስተካከል ያደርገዋል ነው ያሉት።

የዳያስፖራዎቹና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተለመዱ የቱሪስት መስህቦች ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ ያሉ ከተሞችን እንዲጎበኙ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የዳያስፖራዎቹና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዚህ መጠን ወደ አገር ቤት መምጣታቸው የቱሪዝም ፍሰቱን ዓመቱን ሙሉ ለማድረግ የሚሰራውን ሥራ እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በውጭ አገራት የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ - ኢትዮጵያውያን ለመጪው ገና በዓል ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።  

ወደ አገር ቤት ሲመጡ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ የውጭ አገር ዜጋ ይዘው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸውም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም