ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እየተስተዋለ ያለው የውጭ ጣልቃ ገብነት ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚቃረን ነው

ታህሳስ 8/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እየተስተዋለ ያለው የውጭ ጣልቃ ገብነት ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚቃረን መሆኑን በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሻዛብ አባስ ገለፁ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ሻዛብ አባስ፤ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ማንኛውም አይነት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ዓለም አቀፍ ሕግን የሚቃረን ነው ሲሉ ያብራራሉ።

"ማንኛውም አገር በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ይህን አድርጉ አታድርጉ" ብሎ ማዘዝ አይችልም" ይህንንም ሊያደርግ የሚችለው ሲፈቀድለት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

"እኛ በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ የሦስተኛ አገር ጣልቃ ገብነትን አንደግፍም" ይህም ከዓለም አቀፍ አሰራርና ከመንግሥታቱ ድርጅት ቻርታር ጋር የሚቃረን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር ለማቃለል የምታደርገው ጥረት ዓለም አቀፍ ሕግን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸው የፓኪስታን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን መቆሙን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ችግር አገሪቱ በታሪክ ካለፈችበት ችግሮች አኳያ ሲታይ ቀላል ነው፤  ኢትዮጵያ በቅርቡ ከዚህ ችግር እንደምትወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት አሁን ያጋጠመውን ወቅታዊ ፈተና በድል ለመወጣት የሚያስችል ብቃት አላቸው ብለዋል አምባሳደር ሽዘብ።

ኢትዮጵያን በተመለከተ በአንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰራጨው መረጃም ሐሰት መሆኑን ጠቁመው መሬት ላይ ካለው ሃቅ ጋር አይጣጣምም ብለዋል።  

አንዳንድ አገራት ዜጎቻቸው አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ተከታተይ መግለጫ ቢሰጡም ኢትዮጵያን ለቆ ለመሄድ የሚያደርግ አንዳችም ምክንያት አለመኖሩን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባና በሌሎችም በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች የፀጥታ ስጋት በግላቸው አለመመልከታቸውን ጠቁመው ይህንን እውነታ በይበልጥ የማሳወቅ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝቡንና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ደኅንነት ለማረጋገጥ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሮፓጋንዳው የጦርነቱ አካል መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ሻዛብ የኢትዮጵያ መንግሥት ከነዚህ ሁሉ ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚወጣ እምነት አለኝ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም