በ’አንድ ሚሊዮን ወደ የአገር ቤት’ ጥሪ የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዘመቻ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በ’አንድ ሚሊዮን ወደ የአገር ቤት’ ጥሪ የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዘመቻ ተጀመረ
ታህሳስ 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ’አንድ ሚሊዮን ወደ የአገር ቤት’ ጥሪ የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዘመቻ ተጀመረ።
‘አንድ ሻንጣ ለወገኔ’ በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዳያስፖራዎች የመድሃኒት ድጋፍ ይዘው እንዲመጡ የማድረግ አላማ ያለው መሆኑን ኢዜአ ከ’በቃ’ ወይም '#NoMore’ ዘመቻ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ በሺዎች በሚቆጠሩ የጤና ተቋማት ላይ በፈጸመው ውድመትና ዝርፊያ ምክንያት ዜጎችና ተቋማቱ ለችግር መጋለጣቸውን ይታወቃል።
በርካታ ዜጎች የጤና አገልግሎት የሚያገኙባቸው የሕክምና ቁሳቁሶች ስለሚያስፈልጋቸው ወደ አገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችም የሕክምና ግብአቶችን ይዘው እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል።
መድሐኒቶች፣ የሕክምና መሳሪያዎችና ሌሎች የጤና መገልገያ እቃዎችን ይዘው በመምጣት የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖችና የጤና ተቋማት እንዲደርሱ ተጠይቋል።
ወደ አገር ቤት መምጣት የማይችሉ ዳያስፖራዎች ድጋፋቸውን በሌላ ሰው በማስላክ እንዲደግፉ የዘመቻው አስተባባሪዎች ገልጸዋል።
ዳያስፖራው የሚያመጣውን የጤና ቁሳቁስ ድጋፍ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በማሰባሰብ ድጋፉ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንደሚከፋፋልም አመልክተዋል።
እስከ አሁን ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት እንደማይሰጡና በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች ሲካተቱ ዉድመት የደረሰባቸዉ የጤና ተቋማት ቁጥር ከዚህም እንደሚያሻቅብ የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።