የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት አገራቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አሁንም ጠንካራ አንድነት እንዳላት አረጋገጡ

41

ታህሳስ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት አገራቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አሁንም ጠንካራ አንድነት እንዳላት አረጋገጡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በደቡብ ሱዳን ጁባ የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት አካሂደዋል።

በጉብኝታቸውም ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

በውይይታቸውም የሁለቱን አገር ወዳጅነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር አገራቸው ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ደህንነትና የጉርብትና ትብብሩ እንዲጠናከር ጽኑ አቋም እንዳላት ለአቶ ደመቀ አረጋግጠውላቸዋል።

ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገውን ማንኛውንም ጥረት በፍጹም እንደማትቀበል የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር በራሷ የመፍታት አቅም እንዳላት የሚያምኑ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ በበኩላቸው የህግ ማስከበር ዘመቻ የተጀመረበትን ሁኔታ በተመለከተ ማብራሪያ አድርገዋል።

መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት ሊገባ እንደቻለ ገልጸዋል።

ግጭት በተከሰተበት የሰሜኑ ክፍል እየተደረገ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ጥምር ሃይል ባደረገው ዘመቻ በመሬት ላይ ያለው ወቅታዊ ሃቅ እየተቀየረ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ ሁሉን አሳታፊ የሆነ አገራዊ ውይይት ለማካሄድ መታቀዱን የገለጹት አቶ ደመቀ፤ የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው መመለሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም