"የበቃ (No more)" ዘመቻ ከኢትዮጲያውያንም አልፎ አፍሪካዊያንን እያስተሳሰረ ነው

80

ደብረ ታቦር፤ ታህሳስ 7/2014 (ኢዜአ )... "የበቃ (No more)" ዘመቻ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሮች በኢትዮጲያ ላይ እየፈፀሙት ያለውን ያልተገባ ጫና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማሳወቅ ባለፈ አፍሪካዊያንን ለአንድ ዓላማ እያሰለፈ መሆኑን የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።


አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሮች አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ዜጎች  ላይ የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይተው እንዳላዩ እያለፉ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር በዝምታ ማለፋቸው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጣውን ሕጋዊ መንግሥት በሀይል አስወግደው ተላላኪ መንግሥት ለመመስረት ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው ብለዋል።

በሀገር ውስጥና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጲያውያንና ትውልደ ኢትዮጲያውያን የተጀመረው "የበቃ ወይም No more" ዘመቻ  ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ስለሆነ ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጣዕሙ ዓለሙ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በማበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየፈጸመ ያለውን እኩይ ድርጊት በጋራ መመከት ግድ የሚልበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

አሸባሪው ህወሓት የኖረበትን የሐሰት  ፕሮፓጋንዳ ተጠቅሞ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እያደናገረ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ አፍሪካዊያን እያካሄዱት ያለው  "የበቃ" ዘመቻ  ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

እውነቱን እያወቁ ለአሸባሪውን ህወሓት ወግነው  የሐሰት ዜና ሲፈበርኩ የነበሩ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሮችና ዓለም ዓቀፍ የሚዲያ ተቋማት  "የበቃ" ዘመቻው መደናገጥ እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል።

ዘመቻው በኢትዮጰያን ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማሳወቁም በላይ አፍሪካዊያንን አንድ ያደረገ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በአፍሪካ ላይ የሚሰራውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አሻጥር ለመከላከል አህጉራዊ መነቃቃት መፍጠር መጀመሩን አብራርተዋል።

አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሮች አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈጸመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አይተው እንዳላዩ በዝምታ ማለፋቸው ለሽብር ቡድኑ ያላቸውን ውግንና በግልፅ ያሳየ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማት ጦርነት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ብቻ ሳይሆን ከአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሮች ጋር ጭምር ነው ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር አቶ ሰማኸኝ አስማረ ናቸው።

አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሮች ከአሸባሪውን ህወሓት ጋር ያበሩት ኢትዮጵያን አዳክመው ተላላኪ መንግሥት የመፍጠር የረጅም ጊዜ ፕሮጀክታቸውን ለማሳካት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለውን ያልተገባ ጫና ለማስቆም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የጀመሩት "የበቃ " ዘመቻ  ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሀይል በወረራቸው አካባቢዎች ንጹሃንን በጀምላ መጨፍጨፉን፣ ከታዳጊ ሕፃናት እስከ አዛውንት ሴቶች መድፈሩን፣ ማሰቃየቱን፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ማውደሙን እያወቁ በዝምታ ማለፋቸው  መርጦ አልቃሽነታቸውን አሳይቷል ብለዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ሀገሮችን ሴራ ተገንዝቦ ለሀገሩ ዘብ በመቆም  የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስቀጠል አለበት ብለዋል።

አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው ነፃነታቸውን ለማስጠበቅና የአህጉሩን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በጋራ ለማጎልበት የጀመሩት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም