የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የእጅ ኳስ ብሔራዊ ቡድን በምስራቅ አፍሪካ ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ አለፈ

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 በኡጋንዳ ርዕሰ መዲና ካምፓላ እየተካሄደ ባለው የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድር ኢትዮጵያን የወከለው ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፍ ችሏል። የዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር ከግንቦት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ከ18 እና 20 ዓመት በታች በሁለት ብሔራዊ ቡድኖች ተወክላለች። ዛሬ ሶስተኛ ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የኬንያ አቻውን 22 ለ 21 ማሸነፍ ችሏል። ቡድኑ በምድቡ ያደረጋቸውን ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍና አንደኛ በመሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜ መግባቱን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለዋንጫ ለማለፍ ከነገ በስቲያ ከአዘጋጇ ኡጋንዳ ጋር የሚጫወት ይሆናል። ኢትዮጵያን የወከለው ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በተመሳሳይ ሶስቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉ የሚታወስ ነው። ቡድኑ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ ከሶማሊያ አቻው ጋር ያደርጋል። የምስራቅ አፍሪካ የዞን አምስት የታዳጊዎች የእጅ ኳስ ውድድር እስከ ግንቦት 12 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም