የመዲናዋ ወጣቶች ለተፈናቃይ ወገኖችና ለሠራዊቱ ከ24 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ አሰባስበዋል

51

ታህሳስ 7/2014/ኢዜአ/ በሽብር ቡድኑ ህወሓት ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖችና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ከ24 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ በወጣት አደረጃጀቶች መሰባሰቡን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የመዲናዋን ወጣቶችና የስፖርት ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ድጋፉን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ፤ በእስካሁን ሂደት የወጣት አደረጃጀቶችን በማስተባበር ከ24 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነትና የገንዘብ ድጋፍ መሰባሰቡን ተናግረዋል።

በቀጣይም ወጣቶችንና የስፖርት ቤተሰቡን በማሳተፍ በወረራ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በመሄድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

ወጣቶች የአገሪቷ ኢኮኖሚ በተሻለ ሁኔታ እንዲነቃቃ ትርፍ ሠዓታቸውን ለስራ በማዋል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ እየሰራ መሆኑንም የቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም