ኢትዮጵያውያን ሰላማችንን ማስጠበቅና ለዕድገታችን መሥራት ይጠበቅብናል

61

ሰመራ፤ ታኅሣሥ 7/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ተላላኪዎችን በመመከት ሰላማችንን ማስጠበቅና ለዕድገታችን መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ ለአፋር ክልል ተፈናቃይ ወገኖች ከውሃና ኢነርጂ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮች የተለገሰውን ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት፤ ኢትዮጵያውያን ሰላማችንን እያስጠበቅን፣ ለልማትና ለዕድገት መሥራት ይገባናል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን አሸባሪውን ቡድን ሀገራዊ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ላይ ለማድረስ  ከመንግሥት ጎን መቆም ይጠበቅብናል ብለዋል።

በአፋርም ሆነ በአማራ ክልሎች ነጻ በወጡ አካባቢዎች ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ  ይኖርብናል ነው ያሉት ርዕስ መስተዳድሩ።


ዜጎች በአሸባሪው ቡድንና ከጀርባው የተሰለፉ ታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ነቅቶ ከመመከት በተጨማሪ በውስጥ የሽብር ቡድኑ መጠቀሚያ የሚሆኑ ባንዳዎችን አሳልፎ በመስጠት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የአፋር ክልል መንግሥትና ሕዝብ ሀገርን ከጠላት ለመጠበቅ  ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን  በተደራጀ መልኩ የከፈቱትን ዘመቻ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በማክሸፍ እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ እየተጫወቱት ላለው ሚና አድናቆታቸውን ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም