ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የፈጠሩት የዲጂታል ሠራዊት በኢትዮጵያ ፀሃይ እንዳትጠልቅ እያደረገ ነው

ታህሳስ 07/2014(ኢዜአ)  በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በመሰባሰብ የፈጠሩት የዲጂታል ሠራዊት በኢትዮጵያ ሠማይ ፀሃይ እንዳትጠልቅ የሚያደርግ ነው ሲሉ በአሜሪካ የዜጎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ተናገሩ።

ኢዜአ ከአሜሪካ የዜጎች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ እና ከ#NoMore /በቃ/ እንቅስቃሴ አስተባባሪ አቶ ነብዩ አስፋው ጋር በዙም ኢንተርቪው ቆይታ አድርጓል።  

ዲያቆን ዮሴፍ እና አቶ ነብዩ በመላው ዓለም የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላትና የኢትዮጵያን ነፃነት የሚሹ ሁሉ ኢ-ፍትሃዊውን የምዕራባዊያንና አውሮፓዊያን አካሄድ በመታገል ትልቅ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ተከትሎ የተጀመረውን ንቅናቄ በርካታ ለፍትህና ለእውነት የቆሙ ነጮችን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚኖሩ አፍሪካዊያን ዘርፈ ብዙ ትግል እያደረጉ ነው ይላሉ ዲያቆን ዮሴፍ።

ኢትዮጵያ ቀድሞም የነበራትን የነፃነት ትግል ሚና በድጋሚ እውን ለማድረግ በመላው ዓለም የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በመሰባሰብ ወጥና ዘላቂ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም በመላው ዓለም የሚገኙ የዳያስፖራ አባላትና ደጋፊዎች ባሉበት ሆነው ኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ  የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎች ዓለም አቀፍ ጫናዎችን የሚዋጋ ሠራዊት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

የተደራጀው ይህ የዲጂታል ሠራዊትም ቁጥር ወደ 15 ሺህ መጠጋቱንና በተደረገው የኢትዮጵያን እውነት የማስረዳትና ኢ-ፍትሃዊ አካሄድን የመቃወም ትግልም በርካታ ድሎች እየተገኙ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሜሪካ የ"በቃ" እንቅስቃሴ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ነብዩ አስፋው በበኩላቸው ዳያስፖራው አገሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ከመከላከል ባለፈ በአሸባሪው ህወሓት የወደመውን መሰረተ ልማት በአጭር ጊዜ መገንባት የሚያስችል የድጋፍ ንቅናቄም እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለፈጸመው የሰው ሕይወት ማጥፋት፣ ዘረፋና የመሰረተ ልማት ውድመትን ፍትህ እንዲያገኝ የተጀመረው ትግል እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት የተቀናጀና ሁለንተናዊ ነው ያሉት ዲያቆን ዮሴፍም በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት የነበረውን የስም ማጥፋት ተግባር በመመከት ረገድ ትልቅ ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት።

አቶ ነብዩም ኢትዮጵያ ላይ የተጠነሰሰው ሴራ ከዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እስከ አሜሪካ ፓርላማ መሆኑን በመረዳት በአሜሪካ መንግስት ላይ በተፈጠረው የዲፕሎማሲ ጫና ብዙ ውሳኔዎችን ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል የሚለውን የአሸባሪው ህወሓት የሃሰት ሴራ በአሜሪካ ፓርላማ እንዳይፀድቅ መደረጉን ለአብነት የጠቀሱት አቶ ነብዩ የዲጂታል ሠራዊቱ ለእውነት ከሚወግኑ የፓርላማ አባላት ጋር በሚያደርገው ያላሰለሰ የስልክና የኢሜል ዘመቻ ብዙ ውሳኔዎች እያስቀየረ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም