ለትምህርት ወደ ቻይና የሚሄዱ ተማሪዎች የአገሪቷን ብልጽግና ተሞክሮ ይዘው ሊመጡ ይገባል --ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ለትምህርት ወደ ቻይና የሚሄዱ ተማሪዎች የአገሪቷን ብልጽግና ተሞክሮ ይዘው ሊመጡ ይገባል --ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ
አዲስ አበባ ነሐሴ 18/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለትምህርት እድል ወደ ቻይና የሚሄዱ ተማሪዎችን የአገሪቷን ብልጽግና ተሞክሮ ይዘው እንዲመለሱ አሳሰቡ የቻይና መንግስት ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ፣ የሶስተኛ ድግሪ እና የአጫጭር ስልጠናዎች የትምህርት እድል ሰጥቷል። በሸራተን አዲስ በተካሔደው የሽኝትና የምስጋና ፕሮግራም ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የትምህርት እድሉ ተጠቃሚ ተማሪዎች ከቻይና የብልጽግና ምስጢሮችን ለአገራቸው ተሞክሮ ይዘው እንዲመለሱ አሳስበዋል። ተማሪዎቹ በሄዱበት ለአገራቸው አምባሳደር በመሆን እንዲያስተዋውቁና የኢትዮጵያና ቻይናን መልካም ግንኙነት እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል። ኢትዮጵያና ቻይና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷ አሁንም ላበረከተችው የትምህርት እድል ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ቻይና የትምህርት እድሉን ከዚህ በላይ እንድታሳድግ ጠይቀዋል። በኢትየጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ታን ጂያን በበኩላቸው አገራቸውና ኢትዮጵያ ያላቸው ዘርፈ ብዙ አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ሁለቱ አገራት ካላቸው ትስስር መካከል የሰው ኃይል ግንባታ ላይ መስራት አንዱ መሆኑን ጠቁመው ይህም ለኢትዮጵያ እድገት ቁልፍ መሆኑን ጠቁመዋል። ቻይና ከአፍሪካ አገራት ጋር በሰላምና በልማት ዘርፍ በትብብር መስራት እንደምትፈልግም ገልጸዋል። የትምህርት እድል ካገኙት ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢንጅነር ወንድሙ ተክሌ ተማሪዎችን ወክሎ ባስተላለፈው መልዕክት ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን ለአገሪቱ እድገት ጠቃሚ ሀሳቦችን በመቅሰም፣ በባህል ልውውጥና የአገሪቱን ገጽታ በመገንባት ጠንካራ ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግሯል። ምሁራን ለቻይና እድገት ቁልፍ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሶ የዚህ ትምህርት እድል ተጠቃሚዎችም በትምህርት ቆይታቸው ለኢትዮጵያ እድገት የሚበጅ እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም እንዲተጉ አስገንዝቧል፡፡ ቻይና ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በጤና፣ በግብርና፣ በህዝብ አስተዳደር፣ በቱሪዝም ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት፣ በከተማ ልማትና ድህነት ቅነሳ ላይ የአጭርና የረጅም ጊዜ የትምህርት እድል መስጠቷን መረጃዎች ያሳያሉ።