ለሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት በእጩነት የቀረቡት ሙስጠፋ ሙሐመድ ኡማር ማናቸው? - ኢዜአ አማርኛ
ለሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት በእጩነት የቀረቡት ሙስጠፋ ሙሐመድ ኡማር ማናቸው?
አዲስ አበባ ነሃሴ 19/2010 የ45 ዓመቱ ሙስጠፋ ሙሐመድ ኡማር የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ ለመሾም ኢሶሕዴፓ በእጩነት አቅርቧቸዋል። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1973 በሱማሌ ክልል ደገሃቡር ከተማ የተወለዱት አቶ ሙስጠፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ከእንግሊዝ አገር አግኝተዋል። ላለፉት 23 ዓመታትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለያየ የሥራ ዘርፍ አገልግለዋል። ከዚህም ሌላ በኢትዮጵያ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች በቴክኒካልና ሥራ አመራር ደረጃዎች በኃላፊነት ሰርተዋል። በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር ጉዳዮች በተለይም በምግብ ዋስትና መስክ እንዲሁም ኃብት በማሰባሰብና በስትራቴጂያዊ እቅድ ማበልፀግ ዘርፎች የካበተ የሥራ ልምድ አላቸው። ከዚህም ሌላ በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ እርዳታዎች ጉዳይ ማስተባበሪያ መስሪያ ቤትን በመወከል በዚምባብዌ፣ ኬንያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች አገልግለዋል። በተመድ የማስተባበሪያ ቢሮው የሶማሊያ ጉዳይ አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ የነበሩ ሲሆን፤ የሰብዓዊ ጉዳዮች ተሟጋችና ፀሃፊ በመሆንም ይታወቃሉ። አቶ ሙስጠፋ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) ምክትል ሊቀ-መንበር ናቸው። የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) የክልሉን የመንግስት መዋቅር ከላይ እስከታች የማደራጀት ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ከነሀሴ 4 እስከ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ግምገማ ሲያካሂድ ቆይቶ በማጠቃለያው በሰጠው መግለጫ ይፋ አድርጓል። በግምገማው በክልሉ ስለሚታዩ የተለያዩ ችግሮች፣ ውይይት በማድረግ ውጤታማ ውሳኔዎችና በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎችም ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ግብአቶች ማግኘቱን ለኢዜአ አስታውቋል።