ቀጥታ፡

ኮፊ አናን ለአፍሪካ ሰላምና ዕድገት የነበራቸውን ቁርጠኝነት ማስቀጠል ይገባል

አዲስ አበባ  ነሀሴ 18/2010 የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ለአፍሪካ ሰላምና ዕድገት  የነበራቸውን ቁርጠኝነት ማስቀጠል እንደሚገባ ተገለፀ። የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን በ80 ዓመታቸው ከሳምንት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የሚታወስ ነው። በዛሬው ዕለት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ኮፊ አናንን የሚዘክር መርሃ ግብር ተካሄዷል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ኮፊ አናን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በነበሩበት ወቅት የሰሯቸውን ስራዎች አውስተዋል። ኃላፊዎቹ እንደገለጹት  ኮፊ አናን ጡረታ ከወጡ ቡኋላም  ‘የኮፊ አናን ፋውንዴሽንን‘ በማቋቋም በተለይም ለአረጋውያን ድጋፍ በመስጠት በሰላም፣ በትምህርትና በመንገድ ደህንነት ላይ በመስራት ዓለምን ማገልገል አለማቋረጣቸው ተነግሯል። አፍሪካውያን የኮፊ አናን ራዕይ/ሌጋሲ ሊያስቀጥሉ እንደሚገባም ነው የተገለጸው። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ዶክተር ቬራ ሶንግዌ እንዳሉት ˝በአፍሪካ የልማት ስራዎች ላይ ያደረጉት አስተዋጽኦ በተለይም ለአህጉሩ እጅግ ጠቃሚ በሆነው የሚሊኒየም ልማት ግቦች   ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገሩና አገራቱ ግቦቹን በብሄራዊ እቅዶቻቸው ላይ በማካተት  ስራ ላይ እንዲያውሏቸው ማድረግ ችለዋል˝ ነው ያሉት፡፡ "ለአፍሪካ ሰላም ቀጣይነት ያለው ልማትና ለሴቶች መብት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሰሯቸው ሰራዎች ሁሉንም አፍሪካውያንን የሚያኮራ ነው˝ ያሉት በዝግጂቱ የተሳተፉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት(ILO) የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይደሬክተር ጆርጅ ኦኩቶ በበኩላቸው "ሚስተር ኮፊ አናን ከአፍሪካ ድህነትና ረሃብን  ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆንን ያስተማሩና በልማት፣በአካባቢ  ጥበቃ  ብዙ ስራዎች የሰሩ  እና ሁሉም የሰው ልጅ እኩል መሆኑን እንድናምንም አስተምረውናል" ብለዋል፡፡ ኮፊ አናን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1997 እስከ 2006 ሰባተኛው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ በመሆን ያገለገሉና በሰብዓዊ ስራቸው በ2001 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ነበሩ ። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 1996 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ በመሆን የተሾሙት አናን በህይወት ዘመናቸው ለዓለም ፍትሃዊነትና ሰላም በትጋት ሲሰሩ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም