በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም የውስጥ አቅምን አሟጦ መጠቀም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም የውስጥ አቅምን አሟጦ መጠቀም ይገባል
ታህሳስ 6/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በአገር ውስጥ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።
አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች በሕዝብና በግለሰብ ንብረቶች ላይ ዘረፋና ውድመት ፈፅሟል።
በተለይም የሕዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች የሆኑ ኢንደስትሪዎች፣ ጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና መሰል ተቋማትን አውድሟል።
እነዚህን የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ለማቋቋም በአገር ውስጥ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ምሁራን ይገልጻሉ።
በተለይም አሁን ያለውን ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ መደገፍና መልሶ መገንባት ላይ ትኩረት ያደረገ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መከተል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ብርሃኑ ደኑ፤ በጦርነቱ የወደሙት መሰረተ ልማቶች በአጭር ጊዜ ተቋቁመው ወደ ሥራ መግባት እንዳለባቸው ነው የገለጹት።
በተለይም እንደ ጤና ኬላ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የምግብ ፋብሪካዎች የመሰሉ ለኅብረተሰቡ መደበኛ አገልግሎት የሚሰጡ ዋናዋና ተቋማት ቅድሚያ ተስጥቷቸው መሠራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
እነዚህን መሰረተ ልማቶች መልሶ መገንባት የሚያስችል የኢኮኖሚ አቅጣጫ መከተል እንደሚገባ፤ ለዚህም በዋነኝነት የወስጥ ኃብትን መጠቀም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
በውጭ የሚገኘው የዳያስፖራ ማኅበረሰብም እነዚህን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን አገራዊ ጥረት በገንዘብና በእውቀት መደገፍ እንዳለበት ተናግረዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተቋማት የመንግሥትን መልሶ የማቋቋም ጥረት እንዲደግፉ ግፊት ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ነው ዶክተር ብርሃኑ ያሳሰቡት።
ሌላው የኢኮኖሚ ምሁር አቶ ደረጀ ደጀኔ ደግሞ በአገሪቷ የሚገኘው የተማረ የሰው ኃይል የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርግ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው ይላሉ።
ይህን በማድረግ ከውጭ ሙያተኛ ለማስመጣት የሚወጣውን ወጪ መቀነስና የውጭ ምንዛሬውን ለሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ በሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ አገራዊ አቅም ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ይህንንም በጦርነት ውስጥ ያለፉ በርካታ ሃያላን አገራትም ተሞክሮ የሚያሳየው ሃቅ ነው ብለዋል።
ሕዝቡም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከሚያደርገው ሠብዓዊ ድጋፍ ባሻገር መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።