ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልል ህዝቦች ላይ የፈጸመው ዝርፊያና ውድመት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ካለው ጽኑ ፍላጎት የሚመነጭ ነው

ታህሳስ 6/2014/ኢዜአ/  "አሸባሪው ህወሃት በአማራ እና አፋር ክልል ህዝቦች ላይ የፈጸመው ዝርፊያና ውድመት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ካለው ጽኑ ፍላጎት የሚመነጭ ነው" ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል ተፈናቅለው ሰብዓዊ ድጋፋ ለሚሹ ወገኖች የሚውል የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ባደረገበት ወቅት ነው።

አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን በማፍረስ ታላቋን ትግራይ መገንባት በሚል ቅዠት ባለፉት 50 ዓመታት ገደማ የተለያዩ እኩይ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ ከፈጸመው ጥቃት ባሻገር በአማራ እና አፋር ክልል ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት  ማድረሱን ተናግረዋል።

ድርጊቱም አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ካለው ጽኑ ፍላጎት የሚመነጭ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት በአሸባሩ ቡድኑ ወራሪ ኃይሎች ላይ  የኢትዮጵያዊያን የሆነ አንጸባራቂ ድል ማስመዝገቡንም  አመላክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው የደጀንነት ድጋፍ ለሰራዊቱ ከፍተኛ የሞራል አቅም ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ፤ ተቋሙ እስካሁን ባለው ሂደት ለሰራዊቱ 61 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በአፋርና አማራ ክልሎች በአሸባሪ ቡድኑ ውድመት የደረሰባቸውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ በጀት በመመደብ ጥገና እና የመልሶ ግንባታ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

አገልግሎቱን በአጠረ ጊዜ በማስጀመርም ህብረተሰቡን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።

ተቋሙ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም