በማህበራዊ ሚዲያ የጠላቶችን አጀንዳ ከማራገብ ይልቅ አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል

80

ታህሳስ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በማህበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚሰጡትን አጀንዳ ተቀብሎ ከማራገብ አገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ በበጎ ተግባር ላይ እየተሳተፉ ያሉ ወጣቶች አስገነዘቡ።  

የማህበራዊ ትስስር ገፆችን አንድነትን ለሚያጠናክሩና በጎ ስራዎችን ለሚያጎለብቱ ተግባራት ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ በርካታ ፈተናዎች በተደቀኑባት በአሁኑ ወቅት ዜጎች በመተባበር በሚችሉት ሁሉ አገራቸውን መደገፍና ማገዝ አለባቸው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ 'በአቅሜ እኔም ለአገሬ የድርሻዬን እወጣለሁ'፣ 'አንድነት ለኢትዮጵያ'፣ 'ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያን በጎ አድራጊዎች ጥምረት' ሌሎች ስብስቦችን ፈጥረው በጎ ስራዎች ውስጥ ተሰማርተው ይገኛሉ።

ከነዚህ በጎ ስራዎች ውስጥ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን የመደገፍና የማገዝ ተግባር እየፈፀሙ ነው።

ለአገር መከለከያ ሰራዊት ያሰባሰቡትን ድጋፍ ሲያስረክቡ ከነበሩት መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች፣ ሁላችንም ዜጎችን እየደገፍን በማህበራዊ ትስስር ገፆችንም ለአገራችን በጎ ለማድረግ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ካነጋገርናቸው ወጣቶች መካከል ወጣት ገመቺስ ኤጀታ፤ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ተጠቃሚዎች ሁሉ ለአገራችንና ለህዝባችን በጎ ለማድረግ መዘጋጀት አለብን ብሏል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች የሚሰጡትን አጀንዳ ወጣቱ ተቀብሎ ከማራገብ ይልቅ ለአገርና ለህዝብ በሚጠቅም ነገር ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝቧል።

የማሕበራዊ ትስስር ገፆችን አንድነትን ለሚያጸኑ አስተሳሰቦችና በጎ ስራዎች ማዋል ከሁላችንም ይጠበቃል ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

በአባቶች ጥንካሬ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የኖረችው ኢትዮጵያ በጥቂት ራስ ወዳድ 'ሽፍቶችና ባንዳዎች' እንዳትፈርስ አሁን ሃላፊነቱ የእኛ ነው ሲልም ተናግሯል።

ሌላው ወጣት ናታን ባህሩ፣ ወጣቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ልዩነትን የሚያሰፋና ለጠላት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ አስተሳሰቦችን ከማጋራት መቆጠብ አለባቸው ይላል።

የህልውና ዘመቻው መካሄድ ከጀመረ በኋላ አንዳንድ ማሕበራዊ ትስስር ገጾች ወታደራዊ ሚስጥሮችን ጭምር ያባክኑ እንደነበር አስታውሶ፤ ድርጊቱ ሊታረም የሚገባው መሆኑን ጠቅሷል።

በመሆኑም ወጣቶች የማህበራዊ ትስስር ገፆችን ለአገር ልማት፣ ሰላምና አብሮነት ሊጠቀሙበት ይገባል ብሏል።

በተለይ ብዙ ተከታይ ያላቸው የማህበረሰብ አንቂዎች "ከክፋት ይልቅ መልካምነትን፤ ከጥፋት ይልቅ ልማትን አስቀድመው መስራት አለባቸው" ብሏል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም