የሕወሓት የሽብር ቡድን "ወደ መቃብሩ" እየሄደ እንኳ ከውሸት ፕሮፖጋንዳው አልተላቀቀም

71

ታህሳስ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሕወሓት የሽብር ቡድን በወገን ጥምር ጦር "ወደ መቃብሩ" እየሄደ እንኳ ከውሸት ፕሮፖጋንዳው አልተላቀቀም ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ተናገሩ።

ስለጦርነቱ ምንም ዕውቀት የሌላቸው የትግራይ ልጆችን ወደ ጦርነት በመማገድ ላይ ያለው የህወሓት የሽብር ቡድን ከጠያቂነት እንደማያመልጥም ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት "ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ" ብሎ በመነሳት የትግራይ ህፃናትና አዛውንቶችን ጭምር ለጦርነት አሰልፏል።

አሸባሪው ቡድን የትግራይን ወጣቶች፣ ህጻናትና አዛውንት በገፍ አሰልፎ መማገድ ከጀመረ ከአንድ ዓመት ያለፈው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሆኖም የአገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች በጥምረት እየወሰዱት ባለው የተቀናጀ እርምጃ አሸባሪው ያሰለፋቸው ታጣቂዎች "እጅ በመስጠትና በመደምሰስ ላይ ይገኛሉ" ብለዋል።

የሕወሓት የሽብር ቡድን "ወደ መቃብሩ" እየሄደ እንኳ ከውሸት ፕሮፖጋንዳ አለመራቁን የጠቀሱት አቶ ከበደ ፤ "የትግራይ ህዝብ ሊታለልለት አይገባም" ነው ያሉት።

"አዲስ አበባ ለመግባት የሰዓታት ጊዜ ነው የቀረኝ" በሚል ሲያደናግር የከረመው የጥፋት ሃይል አሁን ላይ ደግሞ ሌሎች የማደናገሪያ ፕሮፓጋንዳዎችን ማሰራጨቱን ቀጥሏል ብለዋል።

የሕወሓት የሽብር ቡድን ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ በሚል በቅዥት ወደ ጦርነት ቢገባም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተደመሰሰ ይገኛል ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው።

ኢትዮጵያዊያን አሸባሪውን በመዋጋት፣ ሰራዊቱን በማገዝና በመደገፍ እንዲሁም የውጭ ጫናዎችን በመመከት እያሳዩት ያለው ትግል ታሪክ የማይዘነጋው መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም የትግራይን ልጆች ወደ ጦርነት በማስገባት እያስጨረሰ ያለው አሸባሪው ህወሃት ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ገልጸዋል።

በአሸባሪው ሃይል ልጆቹን የተነጠቀው የትግራይ ህዝብ እንደ ወጡ የቀሩት ልጆቹን "የት አሉ?" ብሎ ይጠይቃቸዋል ብለዋል።ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እውርዳለሁ ብሎ የተነሳው የህወሃት የሽብር ቡድን አሁን ላይ የራሱን የሲኦል መንገድ በማፋጠን ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም