ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ መቀልበስ የሁላችንም ኃላፊነት ነው

ሀዋሳ ፤ ታህሳስ 05/2014 (ኢዜአ)ሀገሪቱ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ መቀልበስና ፍትሕን ማረጋገጥ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከክልሉ  ከፍተኛ አመራር አካላት ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ በሀዋሳ ከተማ እየመከሩ ባሉበት መድረክ ላይ በጦርነቱ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶቿ ጭምር ተቀናጅተው የሚሰሩበት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህንን የህልውና አደጋ መቀልበስና ፍትሕን በማረጋገጥ ኃላፊነታችን መወጣት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያዊያን የጠላት ኃይል እንደተመኘው ከመበታተን ይልቅ አንድነታቸውን አጠናክረው  በጦርነቱ አኩሪ ገድል በመፈፀም ለማንኛውም ምድራዊ ኃይል የማይንበረከኩ የአባቶቻቸው ልጆች መሆናቸውን በተግባር እንዳስመሰከሩ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት።

በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ክብርና ነፃነት በዲፕሎማሲውና በሌሎች የትግል አውዶች በቁርጠኝነት በመሳተፍ እያስመዘገቡ ያሉት ስኬትም ጠቅሰዋል።

ይህ ክብርና ነፃነትን የማስጠበቅ ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን ማንበርከክ እንደማይቻል ለሌሎች ኃይሎችም ጭምር  ትምህርት ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ርስቱ፤ጦርነቱ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁለንተናዊ ተሳትፏችንን  ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።

በሕዝብ ይሁንታ ሥልጣን የያዘው የኢትዮጵያ መንግሥት ራዕይና ግብ ኢትዮጵያዊያንን ዘመን ከፈጀ የጦርነት አዙሪት ማላቀቅና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሆነም ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

የህልውና ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከመደገፉ  በተጓዳኝ  የመንግሥት ተቀዳሚ ዓላማ የሆነውን ዘላቂ ሠላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ የአመራር አካላት ዋነኛ አጀንዳ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን የራሳቸው የሆኑና አንድነታቸውን አፅንተው እንዲቆዩ ያስቻሏቸው ሀገር በቀል የሠላም እሴቶች ባለቤት ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ እነዚህን እሴቶች ማጎልበትና ለዘላቂ ሠላም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከክልሉና ከዞኖች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም