በሰብአዊ ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነው የአሸባሪው ህወሃት አመራር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ከአለም ጤና ድርጅት ፕሬዝዳንትነት ለማስነሳት ያለመ ዘመቻ እየተካሄደ ነው

37

ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነውን አሸባሪው ህወሃትን በውጭ በመምራት ላይ የሚገኘውን ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ከአለም ጤና ድርጅት ፕሬዝዳንትነት ለማስነሳት ያለመ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።

ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን እንዲሁም ኤርትራውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በአለም አቀፍ ደረጃ በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነውን የአሸባሪው ህወሃት ድርጊቶችን ማስረጃ በመያዝ የሽብር ቡድኑን አመራሮች ተጠያቂ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ነው።

በዚህም የአለም ጤና ድርጅት መርህ ከሚያዘው ገለልተኝነት፣ ታማኝነትና ግልጸኝነት ውጪ በመስራት ለአሸባው ህወሃት በውጭ ድጋፍና አመራር በመስጠት ላይ የሚገኘው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምን ተጠይቂ ለማድረግ የፊርማ መሰባሰብ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።

ዶክተር ቴድሮስ አለም አቀፍ ሀላፊነቱን በመጠቀም የሽብር ቡድን በሀገር ውስጥ የሚፈጽማቸውን አለም አቀፍ ወንጀሎች በመሸፈንና ይልቁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሊጠቅሙ የሚችሉ የጤና ተቋማት በሽብር ቡድኑ ሲወድሙ ባላየ በማለፍ ለሽብር ቡድኑ ሽፋን መስጠቱ ዘመቻው ለአለም ጤና ድርጅት በሚልከው የፊርማ ማሰባሰቢያ ዘመቻ አመልክቷል።

አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያን ህጋዊ መንግስት ከስልጣን ለማውረድ በሚያካሂደው እንቅስቃሴም ዶክተር ቴድሮስ አለም አቀፍ ሃላፊነቱን በመጠቀም ድጋፍ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ያመለከተው ዘመቻው ከሃላፊነቱ በመነሳት እንዲጠየቅ አሳስቧል።

በተጨማሪም የሽብር ቡድኑ አመራር ዶክተር ቴድሮስ የጤና ሚኒስቴርን በሚመራበት ወቅት የፈጸማቸውን የተለያዩ ህገ ወጥ ድርጊቶችና በወንጀል የሚያስጠይቁ ጉዳዮችንም ዘመቻው አካቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም