ኮሚሽኑና የጋሞ ዞን ህዝብ ለተፈናቀሉ ወገኖች 44 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ

76

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 4/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽንና የጋሞ ዞን ህዝብ በአማራ ክልል በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች 44 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረጉ።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የርክክብ ሥነ ስርዓት ላይ እንዳሉት አሸባሪው ቡድን በፈፀመው ወረራ በአማራና በአፋር ክልል ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

ኮሚሽኑና ሰራተኞቹ በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያና ለመልሶ ግንባታ የሚውል በጥሬ ገንዘብ 23 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም በክልሉ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ባጋጠመበት ወቅት የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ እስካሁን ድረስ 520 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የአይነት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ  አሸባሪ ቡድኑ እስኪወገድ ድረስ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል ።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው የጋሞ ህዝብ  ከሌሎች ወንድም ህዝብ ጋር በመሆን ጠላትን በመመከት በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደርና ኢትዮጵያዊነቱን ያስመሰከረ ህዝብ መሆኑን  ገልጸዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ከህዝቡ የተሰበሰበ  10 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ ለክልሉ መንግስት አስረክበዋል።

የጋሞ ህዝብ ከአማራ ክልል ህዝብ ጎን በመቆም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ተናግረዋል።

''የአማራ ህዝብ ጥቃት የእኛም ጥቃት ነው ብላችሁ ረጅም ርቀት ተጉዛችሁ በመምጣት ላደረጋችሁት ድጋፍ በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም አመሰግናለሁ'' ብለዋል።

ሀገር ለማፍረስ ቆርጦ የተነሳውን አሸባሪው ህወሓት መላ ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን በማፅናት ዳግም እንዳይነሳ ማስወገድ ይኖርብናል" ብለዋል።

''ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመነሳት አሸባሪውን እንደምናጠፋው አልጠራጠርም'' ሲሉ ዶክተር ይልቃል አስታውቀዋል ።

"የተረከብነውን ድጋፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያና ለመልሶ ግንባታ እንዲውል በአግባቡ እናደርሳለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም