ክልሉ ብሎም ሀገሪቱ ከአሸባሪው ስጋት ነጻ እስኪሆኑ ድረስ የሁሉም የነቃ ተሳትፎ መጠናከር አለበት

47

ሰመራ ፤ ታህሳስ 4/2014(ኢዜአ) ከልሉ ብሎም ሀገሪቱ ከአሸባሪው የህወሃት ቡድን ስጋት ሙሉ ለሙሉ ነጻ እስኪሆኑ ድረስ የሁሉም የነቃ ተሳትፎ በተጀመረው ግለት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ተናገሩ።

በካሳጊታ ግንባር   ለተገኘው  አንጸባራቂ ድል ተሳትፎ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላት ክልላዊ የምስጋና ፕሮግራም ዛሬ በአደአር ወረዳ ተካሄዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሀገሪቱን ገቢና ወጪ ንግድ መስመር ለመቆጣጠር አቅዶ የከፈተው ጦርነት  በወገን ሃይል ተቀልብሶ ጠላት መራር ሽንፈት መጎንጨት ግድ ሆኖበታል።

በግንባር የተገኘው  አንጸባራቂ ድል ክልሉን ብቻም ሳይሆን የአጎራባች ደቡብ ወሎ ወንድሞቻችንን  ብሎም ሀገርን ያኮራ  ታሪካዊ ገድል የተፈጸመበት ነው ብለዋል።

ለዚህም የአፋር ልዩ ሃይልና ሚሊሻ እንዲሁም ህብረተሰቡ በታላቅ ቁርጠኝነት  ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ፊት ለፊት  በመፋለም የተገኘ ድል  በመሆኑ ልትኮሩ ይገባችኋል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

እንዲሁም  ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ሲያስተባብሩ የነበሩ የክልሉ ኮማንድ ፖስት ፣  በየደረጃው የሚገኙ የዞንና የወረዳ አመራር አካላት ሚና ሌላው ለድሉ መገኘት የሚጠቀሱና ሊመሰገን የሚገባቸው መሆናቸውንም አውስተዋል።

የህልውናው ዘመቻ አሁንም የቀጠለ በመሆኑ ክልሉ ብሎም ሀገሪቱ ከአሸባሪውና ወራሪው ጠላት ሙሉ ለሙሉ ነጻ እስኪሆኑ ድረስ የሁሉም የነቃ ተሳትፎ በተጀመረው ግለት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ አወል ተናግረዋል።

በካሳጊታ ግንባር የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ አቶ መሀመድኑር ሳሊም በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ የከፈተው ጦርነት  ሰራዊቱ በጠንካራ ህዝባዊ ደጁን ታግዞ በጀግንነት በመዋደቁ ቀልብሶ የተገኘ ድል ነው ብለዋል።

በተለይም ህብረተሰቡ  አሸባሪውን ፊት ለፊት ከመፋለም ጀምሮ የጠላትን እንቅስቃሴ ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት  ለወገን ሃይል በማድረስ ለድሉ ቁልፍ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።

በግንባሩ ለተገኘው ድል ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እስከ ቀበሌና ጎጥ አመራር ድረስ እንደ አንድ አካል ተናቦና ተቀራርቦ በቁርጠኝነት መሰራት በመቻሉ የተገኘ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኘው አኩሪ ድል እንኳን ደስ አለን  ብለዋል።

በቀጣይም በጦርነቱ የታየው የአመራር፣ ህዝባዊ ንቅናቄና ቁርጠኝነት በልማቱም  መስክ  በመድገም ክልሉንም ሆነ ሀገርን ወደ ብልጽግና ማማ ማሻገር እንደሚገባም ነው አቶ መሀመድ ኑር ያመለከቱት።

በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ አመራሮች፣ የልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት እንዲሁም የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም