ቀጥታ፡

ስልጠናና የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያግዝ 100 ሚሊየን ዩሮ የሚጠጋ የድጋፍ ስምምነት በኢትዮጵያና ጀርመን መካከል ተፈረመ

አዲስ አበባ ነሀሴ 18/2010 ጀርመን በኢትዮጵያ ስልጠናና የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያግዝ 100 ሚሊየን ዩሮ የሚገመት ድጋፍ ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈረመ። ስምምነቱ ዛሬ በኢትዮጵያ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብረሀም ተከስተ እና ከጀርመን አቻቸው ዶክተር ገርድ ሙለር መካከል ነው የተፈረመው። ከፊርማ ስነ ስርዓቱ በኋላ ዶክተር አብረሐም እንደተናገሩት የድጋፉ ዓላማ የኢትዮጵያ ወጣቶች በተለይም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና አግኝተው አነስተኛ ኩባንያ የሚያደራጁበትን ዕድል ለመፍጠር ነው ብለዋል። በስልጠናው በቂ የሙያ ክህሎት አግኝተው የስራ ስምሪት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑም ሁኔታዎችን ማመቻቸት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ከዚህ በፊትም ከጀርመን መንግስት ጋር በተለያዩ መስኮች የትብብር ስምምነት እንዳላት የተናገሩት ሚኒስትሩ ለአብነትም በትምህርት፣ በምግብ ዋስትናና በግብርና ምርታማነት ረገድ የነበረው ትብብር ተጠቃሽ ነው ይላሉ። ''ከምንም በላይ የትብብሩ ትኩረት ወጣቶች ጥራት ያለው ሙያ፣ ችሎታና የቴክኒክ አቅም እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፤ ዝርዝር ጉዳዩ ወደ ተግባር ሲገባ የሚታወቅ ቢሆንም'' ብለዋል ዶክተር አብርሀም። እንደ ዶክተር አብረሀም ገለጻ የትብብር ስምምነቱ በተለይ ጀርመኖች የሚታወቁበትን የሙያ ስልጠና ከኢንዱስትሪ ጋር የማስተሳሰር ልምድንም ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ያግዛል። የጀርመን የኢኮኖሚ ትብብርና የልማት ሚኒስትር ዶክተር ገርድ ሙለር በበኩላቸው የትብብር ስምምነቱ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል። ''ይህ አሁን የተፈራረምነው ወደ 100 ሚሊዮን ዮሮ የሚገመተው የትብብር ስምምነት ስልጠናና የስራ ዕድል ፈጠራ የሚያግዝ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመለወጥም ያግዛል'' ብለዋል ሚኒስትሩ። የጀርመን መንግስት በተለይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የአኮኖሚ ትብብር እንዲያድግ ይሻል ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ትብብር በሁለቱ አገራት የግል ዘርፎች እንዲጠናከረም ቢደረግ የተሻለ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በቅርቡ የምጣኔ ኃብት ዘርፏን ክፍት ማድረጓና ሙስናን በመከለከል ረገድ ያላት አቋም ኢንቨስትመንት ለመሳብ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላት ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት የጀርመን ቴሌኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ቢሳተፉ የሚል ሃሳብ እንዳለቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ በመኪና መለዋወጭ ኢንቨስትመንት ዘርፍም የጀርመን ኩባንያዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ በጥቅሉ ጀርመን አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የጀመሩትን የለውጥ ስራዎች በቅርበት ትደግፋለች ብለው "ኢትዮጵያ የጀርመን ተመራጭ አጋር" መሆኗንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራት ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገች ያለች አገር በመሆኗም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል ሚኒስትሩ። ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ጥቅምት መጨረሻ በጀርመን በሚካሄደው የአፍሪካ ልማት ላይ ባተኮረው ጉባኤ ላይ እንዲገኙም ጋብዘዋቸዋል። ኢትዮጵያ በ2010  በጀት ዓመት ከዓለም ዓቀፍ ተቋማት 95 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድርና እርዳታ ያገኘች ሲሆን ከተለያዩ አገራት መንግስታት ደግሞ 56 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድርና እርዳታ ማግኘቷን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም