ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሕዝብ ድጋፍ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም መላው ኢትዮጵያዊ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

የሽብር ቡድኑ ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ከቀያቸው በግፍ አፈናቅሏል።

በቅርቡም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የፀጥታ ሃይሎች ጥምረት ተጋድሎ ቡድኑ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ ተደርጓል።

ይህን ተከትሎም ከቤት ነብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ድጋፎች እየተተሳበሱ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ፖስታ ያበረከተውን ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የአልባሳት ድጋፍ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተረክበዋል።

ሚኒስትሯ በጦርነቱ ሳቢያ በርካታ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንና ለችግርና ለእንግልት መዳረጋቸውን አንስተዋል።

እነዚህን ዜጎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

እስካሁን ይደረገው በነበረው የዕለት ደራሽ ድጋፍ ሁሉም አካል ሲያደርገው የነበረው ርብርብ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።።

"ኢትዮጵያ አገራችን ችግሮችን የምትሻገረውና አሁን ከገባችበት አጣብቂኝ የምትወጣው በጋራ ስንቆም ነው" ሲሉም አክለዋል።

የሽብር ቡድኑ ያደረሰው ሠብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በሰው አዕምሮ የሚገመት አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ ይህን የኅብረተሰቡን ኑሮ የማመሰቃቀልና አገር የማፍረስ ተልዕኮ ለማምከን በአንድነት ልንቆም ይገባል ብለዋል።

በተቀናጀ መንገድ የሚደረግ ድጋፍ በሚያስፈልግበት ቦታ እንዲደርስ ጭምር እንደሚረዳ ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

የኢትዮጵያ ፖስታ አመራሮችና ሠራተኞች 'እኛም በዚህኛው ግንባር ደጀን ነን' በማለት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

ድጋፉ በሁለቱም ክልሎች ለሚገኙ ጥቃት ለተፈጸመባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በዋናነትም ለሴቶች፣ ለሕጻናት፣ ለአረጋዊያንና ለአካል ጉዳተኞች እንደሚደርስ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሃና አርአያስላሴ በበኩላቸው ተቋሙ ቀደም ሲል ለመከላከያ ሠራዊት 5 ሚሊዮን ብር ማበርከቱንና ድጋፉን በሁሉም ዘርፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም ዜጋ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም