ሀሰተኛ መረጃዎች በተበራከቱበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉ ባለሙያዎችን ማፍራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል

65

ታህሳስ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀሰተኛ መረጃዎች በተበራከቱበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛ መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የሚያደርጉ ባለሙያዎችን ማፍራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን ላይ ተግባቦትን በመፍጠር ረገድ አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ከአስር የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና መስጠት በጀመረበት መድረክ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነው።

ስልጠናው በዋናነት በመልዕክት ቀረጻና ንግግር ጽሁፍ፣ በትንታኔና የሀተታ ጽሁፍ እንዲሁም በመጽሄትና ህትመት ውጤቶች አዘገጃጀት ላይ ያተኮረ ነው።

በተጨማሪም ስልጠናው በምስልና ድምጽ ቀረጻ ቴክኒኮች፣ በምስልና ድምጽ ቅንብርና በተቋማዊ መለያ ወይም "ብራንዲንግ" ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ በዚሁ ወቅት፣ ስልጠናው ሙያተኞቹ በልምድና በትምህርት ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተሻለ መልኩ እንዲጠቀሙበት ያግዛል ብለዋል።

አንጋፈው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን ተከትሎ ለህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ስልጠና ማዘጋጀቱንም አድንቀዋል፡፡

አሁን ያለውን ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን ተከትሎ ምንጫቸው የማይታወቅ በርካታ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያነሱት።

ከዚህ አኳያ የመንግስት ተቋማት በተለይ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረው፤ ለዚህ ደግሞ የሙያ ክህሎታቸው ሊዳብር ይገባል ነው ያሉት፡፡

በኢዜአ ተነሳሽነት የተጀመረው ይህ ስልጠና እንደ መንግስት ኮሙኒኬሽን ሊሰራበት የሚገባ በመሆኑ በቀጣይ ዘርፉን የምናግዝ ይሆናል ሲሉ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሠይፈ ደርቤ፤ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በአሁን ወቅት ያሉትን ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ተገንዝብው ስራቸውን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰው፤ ስልጠናው ይህን ባገናዘበ መልኩ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ''ኢዜአ ዋና ዋና ከሚባሉት የፌዴራል የመንግስት ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ቢሰራ አንድ እርምጃ ያግዛል'' በሚል እምነት ስልጠናው መጀመሩንም አንስተዋል።

በመሆኑም ስልጠናው ተቋማቸውን ብሎም አገራቸውን በተሻለ መልኩ በሙያቸው እንዲያገለግሉ እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የስልጠና ምክርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ አብዱራማን ናስር፤ ስልጠናው እየተሰጠ ያለው በተለይ ኢዜአ ከተቋቋመበት ዓላማና ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች በመነሳት እንደሆነ ተናግረዋል።

የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ባሉ የእውቀትና የቴክኒክ ዘርፎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም