በጃማይካ የሚገኙ ራስተፈሪያንና የፓን አፍሪካ አቀንቃኞች ከኢትዮጵያ ጋር ቆመዋል

41

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 04/2014(ኢዜአ) በጃማይካ የሚገኙ ራስተፈሪያንና የፓን አፍሪካ አቀንቃኞች የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫናን በመቃወም ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር መቆማቸውን በተግባር አሳዩ።

በጃማይካ ኪንግስተን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት 'ራስተፈሪያንና ኢትዮጵያዊያን የበቃ #NoMore' የተቃውሞ ሰልፍ አካሄደዋል።  

በሰልፉም ጃማይካ የሚገኙ ራስተፈሪያንና የፓን አፍሪካ አቀንቃኞች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጋር መቆማቸውን በተግባር አሳይተዋል።

በ"በቃ" የንቅናቄ ዘመቻው አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት በመቃወም ድምፃቸውን አሰምተዋል።

'አሜሪካና አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሱ፣ ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ጉዳዮች በራሷ አቅም መፍታት ትችላለች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአሸባሪውን ሕወሓት ድርጊት ማውገዝ አለበት’ የሚሉና ሌሎች መልዕክቶችን አስተላለፈዋል።

ሰልፉ የተዘጋጀው 'ራስተፈሪያን'ና ኢትዮጵያዊያኑ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጎን መቆማቸውን ለማሳየት መሆኑን በሰልፉ የታደሙት ዮዲት ጌታቸው ተናግረዋል።

በተለይም አሜሪካና አንዳንድ የምዕራብ አገራት በህዝብ ምርጫ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት እውቅና በመንፈግ ለአሸባሪው ቡድን የሚያደርጉትን ድጋፍ ሠልፈኞቹ አውግዘዋል።

አሜሪካና አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያራምዱት የሐሰት መረጃና ፕሮፓጋንዳ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመጉዳት ታስቦ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው የሰልፉ ታዳሚ ራስ ካሌብ፤ በምርጫ በኢትዮጵያ ሕጋዊና ዴሞክራሲዊ መንግሥት ከተመሰረተ ማግስት ጀምሮ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራብ አገራት ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና ተገቢ ባለመሆኑ እጃቸውንም ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ለመጠየቅ ወጥተናል ብሏል።    

አሜሪካ ኢትዮጵያን ለማዳከም የምታደርገውን ያልተገባ የፖለቲካ ጫና እና ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ኢኮኖሚ ጫና ለመቃወም እንዲወጡ የሚገልጹት ደግሞ ከሰልፉ ታዳሚዎች መካከል አንቶኒይ ሂልቶን ናቸው።

የአገራቱ ጫና እና ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ለአፍሪካ አገራት የሚያቀርበውን ከቀረጥና ከታሪፍ ነጻ የንግድ እድል (አጎዋ) ኢትዮጵያን ማስወጣቷ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

በሰልፉ ላይ የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ ግዛት ንቅናቄ (ፓን አፍሪካኒዝም) አቀንቃኞችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም