ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በህዝብ ላይ ይቅር የማይባል አሰቃቂ ግፍና በደል ፈፅሟል

ታህሳስ 03/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በአማራ ክልል በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በህዝብ ላይ ይቅር የማይባል አሰቃቂ ግፍና በደል መፈጸሙን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አሸባሪው ቡድን በደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ በደሴና በቦሩ ሜዳ ሆስፒታሎች ላይ ያደረሰውን ውድመት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉትም አሸባሪውና ወራሪው ሃይል በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ንፁሃንን በመግደል፣ የመንግስትና የግለሰብ ንብረቶችን በመዝረፍ የአገርና የህዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።

በአማራ ክልል በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በዜጎች ላይ ግድያ ከመፈፀም በተጨማሪ ሴቶችን በመድፈር ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ያሳደረ ሲሆን በኢኮኖሚ ለማዳከም የፈፀመው ዘረፋና ውድመትም መጠነ ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህንን አገር ለማፍረስ የተንቀሳቀሰ ሃይል ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር ያደረገው ተጋድሎ የላቀ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ወጣቱ ሰራዊቱን በመቀላቀል፣ በመደገፍና በማገዝ ያሳየው ቁርጠኝነት ድንቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በፀጥታ ኃይሎች ጥምረት አከርካሪው የተሰበረው አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ዳግም እንዳይነሳ ተደርጎ እየተመታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ህዝብ ከመላ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተባበር አሸባሪው ህወሃት የዘረፋቸውንና ያወደማቸውን ተቋማት መልሶ መገንባት አለበት ብለዋል።

የወደሙ ተቋማት በትብብር በፍጥነት ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ ርእሰ መስተዳድሩ የሁሉንም ተሳትፎና ድጋፍ ጠይቀዋል።

አሸባሪው ያደረሰውን ውድመት መልሶ ከመገንባት ባለፈ ነዋሪው አደረጃጀቱን በማጠናከር በየአካባቢው ሰላሙን መጠበቅ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም