የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ባለፉት አምስት ወራት ከእቅድ በላይ አሳክቷል

97


ታህሳስ 03/2014 (ኢዜአ) የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ባለፉት አምስት ወራት የእቅዳቸውን 120 በመቶ ማሳካታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ በሞጆ እና አዳማ የሚገኙ የቆዳ እና የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።

የዘርፉን እንቅስቃሴ ወቅት የተመለከቱት ሚኒስትሩ ባለፉት አምስት ወራት 80 የሚደርሱ መካከለኛና ከፍተኛ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።

ይህም በቀጣይ የተሻለ ስራ ቢሰራ የአገርን ኢኮኖሚ የመደገፍ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉት ችግሮችን በመፍታት ለአገር ኢኮኖሚ እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማጠናከር መንግስት በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑን ጠቅሰዋል።

የጉብኝቱ ዋነኛ ዓላማም የግል ተቋማትን በቅርበት ለመደገፍና ለማበረታት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የተናገሩት አቶ መላኩ፤ በተለይም የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን ምርት ለማሳደግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ 27 የሚደርሱ መካከለኛና ከፍተኛ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ከእነዚህም 19 የሚሆኑት የተሻለ ምርት በማምረት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በአገሪቱ ከሚገኙ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች 90 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ገልጸው ባለፉት አምስት ወራት የእቅዱን 73 በመቶ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም