በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ እንተጋለን

63

ድሬዳዋ፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገርን የማዳን ህብረ-ብሔራዊ ዘመቻ በስኬት ተደምድሞ የኢትዮጵያ አሸናፊነት እስኪረጋገጥ ድረስ የተጀመረው ድጋፍ እንዲጠናከር እንደሚተጋ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከ650 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የእርድ አንስሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ዛሬ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርጓል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በወቅቱ እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያን ከፍታና የማህበረሰቡን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከወትሮው በተለየ ቁርጠኝነት የተለያዩ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች እያካሄደ ነው።

እነዚህ የተቋሙ ተግባራት በስኬት የሚጠናቀቁትንና የመማር ማስተማር ስራው ፍሬ የሚያፈራው የሀገርን ህልውና በተቀናጀ መንገድ መጠበቅ ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።

የሀገርን ህልውና ለማስጠበቅ በግንባር እየተዋደቀ ላለው የመከላከያ ሠራዊት ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገው ድጋፍ እስከመጨረሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጥዋል።

ድጋፉን የተረከቡት ኮሎኔል ጌታነት አየነው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያን ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም እያደረጉት ያለው ሀገር የማዳን ርብርብ ለሠራዊቱ ተልዕኮ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

"የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከጎናቸው በመሆን በሙያ፣ በምግብና በቁሶች እያደረገ ያለው ድጋፍ በአርያነት የሚጠቀስ ነው" ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ሠራተኞችና አመራሮች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም በመለገስ ደጀንነታቸውን አሳይተዋል።

በተጨማሪ ከ60 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ያዘጋጁትን ስንቅ፣ የንፁህና መጠበቂያ ቁሶች እና ቴምር ለሠራዊቱ አስረከብዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም