የኦዲት ክፍተት የተገኘባቸው ተቋማት ፈጥነው ከችግራቸው እንዲወጡ ይሰራል

29

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦዲት ክፍተት የተገኘባቸውን ተቋማት ፈጥነው ከችግራቸው እንዲወጡ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በትኩረት እንደሚሰራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ ገለጹ።

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር ለቋሚ ኮሚቴ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ በወቅቱ እንዳሉት፤  በኦዲት ግኝት መሰረት ተቋማት ካላቸው ውስንነት ወጥተው ለህዝብ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ እንዲሰሩ ክትትል ይደረጋል።

ቋሚ ኮሚቴው በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ በዋና ኦዲተር በኩል  የኦዲት ግኝት ያለባቸውን ተቋማት በመለየት የድጋፍና ክትትል ስራዎች እንደሚያከናወን ገልጸዋል።

የኦዲት ክፍተት የተገኘባቸው ተቋማት ፈጥነው ከችግራቸው እንዲወጡ ቋሚ ኮሚቴው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት የ26 ተቋማትን የፋይናንስ ክዋኔ የህዝብ አስተያየትን ለማድመጥ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በ12 ተቋማት ላይ ደግሞ የመስክ ምልከታ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

የመንግስት ተቋማት ህግንና ስርዓትን የተከተለ የበጀት አጠቃቀም ሂደትን እንዲከተሉ ከማገዝ ባለፈ ተቋማት በሚያከናውኗቸው ተግባራት የህዝብን ተጠቃሚነት እንዲያሳድጉ በቋሚ ኮሚቴው በኩል በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

ተደጋጋሚ እድል ተሰጥቷቸው መስተካከል ያልቻሉ ተቋማት ላይ ቋሚ ኮሚቴው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን ጠቁመዋል።

ለዚህም ህዝቡ በአገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችንና መልካም ተግባራትን መጠቆም እንደሚገባው ጠቁመዋል።

የፌደራሉ ዋና ኦዲተር የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ የኦዲት ግኝት ያላቸው ተቋማት ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን የባለድርሻ አካላት ተግባርና ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

የመንግስት መስሪያ ቤቶች የበጀት አጠቃቀማቸውን ህግንና ስርዓትን ተከትለው እንዲሰሩ ለማስቻልም የቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ድጋፍ ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም